Back to top

Sabbath Bible Lessons

ከየሱስ ጋር መራመድ

 <<    >> 
ሰንበት፣ መስከረም 02፣ 2019 11ኛ ትምህርት
የጸሎት በረከት የመታሰቢያ ጥቅስ፡- “አንተ ግን ስትጸልይ፥ ወደ እልፍኝህ ግባ መዝጊያህንም ዘግተህ በስውር ላለው አባትህ ጸልይ፤ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከፍልሃል።” (ማቴዎስ 6፡6)።
ለንባብ የተመረጠው መጽሐፍ ፡   Steps to Christ, chapter 11፣ pp. 93–104። 
“ለወዳጅ የልብን እንደሚያጫውቱ ጸሎትም ለእግዚአብሔር የልብን ማጫወት ነው። የምንጸልየው ስለ እኛ ሁኔታ ለእግዚአብሔር የሚያውቀውን መረጃ ለመስጠት ሳይሆን፤ እርሱን በልባችን ለመቀበል እንዲያግዘን ነው። ጸሎት እግዚአብሔርን ወደ እኛ እያወርደውም፤ ነገር ግን እኛን ወደ እርሱ ከፍ ያደርገናል።”—Steps to Christ, p. 93

1. ታላቁ ጸላይ (THE GREAT SUPPLIANT) እሁድ ፣ ጷጉሜ 01
ሀ. የሱስ የሰው ልጅ እንደመሆኑ መጠን ምን አስፈላጊ ሆኖ አግኝቶታል? ሉቃስ 5:16ማርቆስ 6:46 “ እነሆ የእግዚአብሔር ልጅ ወደ አባቱ ለመጸለይ ሲንበረከክ ተመልከቱት! ምንም እንኳን የእግዚአብሔር ልጅ ቢሆንም፣ በጸሎት እምነቱን ያጠናክራል፣ ከሰማይ ጋር በመገናኘት (በመተባበር) ክፋትን ለመቋቋምና የሰዎችን ፍላጎት ለማሟላት ኃይልን ይቀበላል። የሰብዓዊ ዘር ታላቅ ወንድም እንደመሆኑ፣ በድካም (በችግር ውስጥ) የተከበቡትን እና በኃጢአትና በፈተና በተሞላ ዓለም ውስጥ እየኖሩ እንኳን እርሱን ለማገልገል የሚፈልጉትን ምን እንደሚያሻቸው ያውቃል። የሚልካቸው መልእክተኞች ደካማና የሚሳሳቱ ሰዎች መሆናቸውንም ያውቃል፤ ነገር ግን ራሳቸውን ሙሉ በሙሉ ለአገልግሎቱ ለሚሰጡ ሁሉ መለኮታዊ እርዳታ እንደሚሰጥ ቃል ገብቷል። የእርሱ የራሱ ምሳሌ በእምነት ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ ልባዊና የማይሰለች ጽኑ ልመና ማለትም በእግዚአብሔር ላይ ሙሉ በሙሉ ወደመታመን እና ራሳቸውን ሙሉ በሙሉ ለሥራው እንዲሰጡ በሚያደርግ እምነት የሚቀርብ ልመና፣ ከኃጢአት ጋር በሚደረገው ውጊያ የመንፈስ ቅዱስን እርዳታ ለሰዎች እንደሚያመጣላቸው ማረጋገጫ ነው።”—Gospel Workers, p. 511 ለ. የክርስቶስ የጸሎት ልምምድ ለእኛ ምሳሌ የሚሆነው እንዴት ነው? ማርቆስ 1:35ሉቃስ 6:12 “የሱስ ራሱ በሰዎች መካከል በኖረ ጊዜ ጸሎትን አዘውትሮ ተለማምዶአል።”—Steps to Christ, p. 93

2. የክርስቶስ ጸሎት ሰኞ ፣ ጷጉሜ 02
ሀ. የሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንዴት እንዲጸልዩ አስተማራቸው? ሉቃስ 11:1-4 “የሱስ በምድር ላይ በነበረ ጊዜ ደቀመዛሙርቱን እንዴት መጸለይ እንዳለባቸው አስተማራቸው። እለታዊ ፍላጎታቸውን ሁሉ በእግዚአብሔርፊት እንዲያቀርቡና የሚያስጨንቃቸውን ሁሉ በእርሱ ላይ እንዲጥሉት መራቸው። ልመናቸው እንደሚሰማ የሰጣቸው ዋስትና ለእኛም ጭምር ነው።”“አዳኞችን ፍላጎቶቻችንንና ድካማችንን ተጋርቶ ስለነበር፣ ስራውን ለመስራትና ፈተናን ለመጋፈጥ እንዲችል አባቱ ጥንካሬ እንዲሰጠው ይለምን ነበር። እርሱ በሁሉ ነገር ምሳሌያችን ነው። “በሁሉ እንደእኛ የተፈተነ፡ ወንድማችን ሲሆን ምንም ኃጢአት የሌለበትና ስብዕናውም ለኃጢአት ጀርባውን የሰጠ ነበር። በኀጢአት በተሞላች ዓለም ውስጥ ያለውን ትግልና የነፍስ ስቃይ በትእግስት አልፎታል። በለበሰው ሰብአዊ ተፈጥሮ የተነሳ ጸሎት ለእርሱ አስፈላጊና ደግሞም የበረከት ምንጭ ነበር። ከአባቱ ጋር በሚያደርገው ግንኙነት ደስታና መጽናናትን ያገኝ ነበር። ታዲያ የሰው ልጆች አዳኝ ለሆነው የእግዚአብሔር ልጅ ጸሎት እንዲህ ካስፈለገው፣ ደካማና ሟች ለሆኑት ኃጢአተኛ ፍጡራን ምን ያህል በበለጠ ብርቱና ቋሚ ጸሎት ያስፈልጋቸው ይሆን!”—Steps to Christ, pp. 93, 94 ለ. መጽሐፍ ቅዱስ ስለክርስቶስ ጸሎት እና ይህ በጣም አስፈላጊ የሆነበትን ምክንያት እንዴት ይገልጸዋል? ኢሳይያስ 50:4ዕብራውያን 2:10፤ 5: 7-9። “እንደ ሰው በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ፣ ከአባቱ ብርታትን ማግኘት እንዳለበት ተሰማው። የተመረጡ የጸሎት ቦታዎች ነበሩት። በተራራው ብቻውን ከአባቱ ጋር ኅብረት ማድረግ ይወድ ነበር። በዚህ ልምምድ፣ ቅዱስ፣ ሰብዓዊ ነፍሱ ለቀኑ ተግባራትና ፈተናዎች ተጠናከረ። አዳኛችን ራሱን ከፍላጎቶቻችንና ከድክመቶቻችን ጋር አንድ አድርጓል ፤ በዚያም ልመና የሚያቀርብ፣ በሌሊት በፀሎት የሚቃትት በመሆን፣ ተበረታቶና ታድሶ ይወጣ ዘንድ ከአባቱ ትኩስ ኃይልን በመሻት፣ ለቀኑ ለሥራና ለፈተና ይዘጋጅ ነበር። እርሱ በሁሉም ነገር ምሳሌያችን ነው።”—Testimonies for the Church, vol. 2, pp. 201, 202.“ከሀያ ወጣቶች ውስጥ ተገባራዊ ኃይማኖት ምን እንደሆነ የሚያውቅ አንድም እንኳን እንደሌለ ተመለከትኩ። ራሳቸውን እያገለገሉ ሳለ፣ ነገር ግን የክርስቶስ አገልጋዮች ነን ይላሉ ፤ ዳሩ ግን በእነሱ ላይ ያለው አፍዝ አደንግዝ ካልተሰበረ፣ የሕግ ተላላፊው ድርሻ (እጣ ፈንታ) የእነሱ እንደሚሆን በቅርቡ ይገነዘባሉ። ለእውነት ሲባል ራስ-መካድን ወይም የራስ ጥቅምን መስዋዕት ማድረግን በተመለከተ፣ ከዚህ ሁሉ በላይ (ሌላ) ቀለል ያለ መንገድ አግኝተዋል። ስለ ይቅር ባይ ጸጋው እና የሰይጣንን ፈተናዎች ለመቋቋም ከእርሱ የሚመጣን ጥንካሬ ለማግኘት በእንባ እና በጠንካራ ጩኸት ወደ እግዚአብሔር ልባዊ ልመና (ተማጽዕኖ) ማቅረብን በተመለከተ፣ በትጋት መሞላትና በጣም ቅንዓት ማሳየት እምብዛም አስፈላጊ አድርገው አላዩትም፤ ያለጸሎት ከአምላክ ጋር ጥሩ ግንኙነት ሊኖራቸው እንደሚችሉ ያስባሉ። የክብር ንጉሥ የሆነው ክርስቶስ፣ የነፍሱን ልመና ለአባቱ ለማፍሰስ ብዙ ጊዜ ወደ ተራሮች እና በረሃማ ቦታዎች ብቻውን ይሄድ ነበር ፤ ነገር ግን ኃይል የሌለው ኃጢአተኛ ሰው በጣም ብዙ ጸሎት ሳያደርግ መኖር እንደሚችል ያስባል።”—Ibid., vol. 1, pp. 504, 505.

3. የጸሎት ልዩ ጥቅም ማክሰኞ ፣ ጷጉሜ 03
ሀ. የሱስ ስለሰው ልጅ ፍላጎት ያለውን የአባቱን ሃሳብ እንዴት ገለጠልን? ማቴዎስ 6:6፤ 7:7-11 “በሰማይ ያለው አባታችን የበረከቱን ሙላት በእኛ ላይ ሊያወርድ እየተጠባበቀ ይገኛል። ወደር ከሌለው የፍቅር ምንጭ የፈለግነውን ያህል የመጠጣት መብት ተሰጥቶናል። ታዲያ ከዚህ የከበረ ዕድል አንጻር ሲታይ፣ በትንሹ መጸለያችን እንዴት የሚገርም ነው! እግዚአብሔር ከልጆቹ መካከል በጣም የደካማውን ሰው ልባዊ ጸሎት እንኳን ለመስማት ፈቃደኛና ዝግጁ ነው። ይህም ሆኖ ግን ፍላጎቶቻችንን በእግዚአብሔር ዘንድ ለማቅረብ ብዙ ስንፍና ተጠናውቶናል። ...“እግዚአብሔር ጥበቡ ጥልቅ ነውና አይሳሳትም፤ መልካምነቱም ታላቅ ነውና በቅንነት ለሚመላለሱት ምንም መልካም ነገር አያጎልባቸውም። እንግዲያውስ ለጸሎታችሁ አፋጣኝ ምላሽ ባታዩም እንኳን በእርሱ ለመታመን አትፍሩ። ‹‹ጠይቁ ይሰጣችኋል›› በሚለው የታመነው የተስፋ ቃሉ ተደገፉ።”—Steps to Christ, p. 94, 96 ለ. ልመናችን በእግዚአብሔር ዘንድ እንዳይሰማ የሚከለክለው ምንድን ነው? መዝሙር 66:18ምሳሌ 28:13 “ሀሳባችን ወደ እርሱ ሊሳብ ይችል ይሆናል፤ ስለ እጁ ስራዎች፤ ስለ ምህረቱ፤ ስለባርኮቱ እናሰላስል ይሆናል፣ በዚህ ብቻ ግን ከእግዚአብሔር ጋር በሙላት ተገናኝተናል ለማለት አይቻልም። ከዚህ በተጨማሪ፣ ስለ አለንበት ትክክለኛ ሁኔታ ለእርሱ የምንናገረው ነገር ሊኖረን ይገባል። . . .“ወደር በሌለው ፍቅር የተሞላው የእግዚአብሔር ልብ፣ ከጠየቁት ወይም ከሚያስቡት ሁሉ በላይ ሊባርካቸው እጅግ ጓጉቶ ሳለ፣ በትንሹ ብቻ ስለሚጸልዩትና እምነታቸውም ደካማ ስለሆነው ለፈተና ስለተጋለጡት፤ ምስኪንና ረዳተቢስ የሰው ልጆች መላእክት ምን ያስቡ ይሆን? መላእክት በእግዚአብሔር ፊት መስገድ ይወዳሉ ወደ እርሱም መጠጋት ደስታቸው ነው። ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት ማድረግን እንደ ትልቅ ባርኮት ነው የሚቆጥሩት፡ እግዚአብሔር ብቻ የሚሰጠው እርዳታ በጣም የሚያስፈልጋቸው ምድራዊ ልጆች ግን ያለ የእግዚአብሔር መንፈስ ብርሃንና፤ ያለ ጌታ አጀብ መንገዳቸውን በማድረግ የረኩ ይመስላሉ።”“መጸለይን ቸል የሚሉ ሁሉ የክፉው ጨለማ ይከብባቸዋል። የጠላት የፈተና ሹክሹክታ ወደ ኃጢአት ይመራቸዋል። ይህ ሁሉ የሚሆነው ታዲያ እግዚአብሔር በጸሎት ውስጥ ያስቀመጠውን በረከት ስላልተጠቀሙበት ነው። …”“ክፋትን በልባችን ከሰወርን፣ ሙጥኝ ያልነው (አጥብቀን የያዝነው) የታወቀ ኀጢአት ካለ፣ እግዚአብሔር አይሰማንም። ስለ ኃጢአቱ የሚናዘዘውንና ራሱን የሚያዋርደውን ነፍስ ጸሎት ግን ጌታ ሁልጊዜ ይቀበላል። የምናውቃቸውን የተበላሹ ነገሮቻችንን ስናስተካክል፣ እግዚአብሔር ደግሞ ልመናችንን እንደሚሰማ ልናምን እንችላለን። የእኛ መልካም ሥራ መቼም ቢሆን በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ እንድናገኝ አያደርገንም። የሚያድነን የክርስቶስ ብቃት ነው፤ የሚያነጻንም ደሙ ነው። ነገር ግን እነዚህን ነገሮች የራሳችን አድርገን በመቀበል ረገድ ልንሰራው የሚገባን ስራ አለ።”—ibid, pp 93–95.

4 አሸናፊ ጸሎት ረቡዕ ፣ ጷጉሜ 04
ሀ. ከደካማና ውጤታማ ካልሆነ ጸሎት ጋር ሲነጻጸር በአሸናፊ ጸሎት ውስጥ ያሉት የጸሎቱ ዋና ዋና ነገሮች ምንድን ናቸው? ዕብራውያን 11:6ማርቆስ 11:24 “የጠየቅነውን ነገር፣ በጠየቅነው ጊዜ ማግኘት ሳንችል ብንቀር እንኳ፣ ጌታ ጸሎታችንን እንደሰማና ደግሞም እንደሚመልሰው ማመናችንን መቀጠል አለብን። አርቀን የማናይና በቀላሉም የምንስት ከመሆናችን የተነሳ፣ አንዳንዴ ሊባርኩን የማይችሉ ነገሮችን እንጠይቃለን። ይሁን እንጂ የሰማዩ አባታችን ለጸሎታችን መልስ አድርጎ በፍቅሩ የሚሰጠን፣ የነገሮችን ትክክለኛ ምንነት ማየት የምንችልበትን መለኮታዊ ማስተዋል ቢሰጠን ኖሮ የምንመርጠውን፣ እጅግ የሚጠቅመንን ነገር ብቻ ነው። ጸሎታችን ያልተመለሰ ሲመስለን፣ የሚመለስበት ጊዜ በእርግጥ ይመጣልና፣ የተስፋውን ቃል ልንጠማጠም ይገባል። በጣም የሚያስፈልገንን ባርኮትም እንቀበላለን።”—Steps to Christ, p. 96 ለ. ጸሎት በጌታ ዘንድ እንዲሰማ፣ ምን ዓይነት መንፈስ ሊኖረን ይገባል? ማቴዎስ 6:12ማርቆስ 11:25፣ 26 “ከእግዚአብሔር ምህረትንና ባርኮትን ለመጠየት ስንቀርብ፣ በልባችን የፍቅርና የይቅርባይነት መንፈስ ሊኖረን ይገባል። “እኛ የበደሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን ይቅር በለን” [ማቴዎስ 6:12] በማለት እየጸለይን፣ ይቅር የማይል መንፈስ እንዴት ሊኖረን ይችላል? የእኛ ጸሎት እንዲሰማ የምንፈልግ ከሆነ እኛ ይቅር ለመባል በምንፈልገው መንገድና በዚያው መጠን ይቅር ልንል ይገባል።”—ibid, p 97 [Author’s italics.] ሐ. ዝናብ እንዲዘንብ ካቀረበው ከኤልያስ ጸሎት ምን እንማራለን ? 1ኛ ነገሥት 18: 41–45 “ ኤልያስ ሲጸልይ አገልጋዩ ተመለከተ። ስድስት ጊዜ ለመመልከት በወጣ ጊዜ “ምንም የለም፣ ደመና የለም፣ የዝናብም ምልክት የለም” እያለ ተመለሰ። ነቢዩ ግን ተስፋ አልቆረጠም። እግዚአብሔርን ለማክበር ያልቻለበትን የሕይወቱን ክፍል ለማየት ሕይወቱን መገምገሙን ቀጠለ፣ ኃጢአቱን ተናዘዘ፣ በዚህም ጸሎቱ መልስ እንዳገኘ የሚያሳይ ምልክት እየጠበቀ ነፍሱን በእግዚአብሔር ፊት ማሰቃየቱን ቀጠለ። ልቡን ሲመረምር፣ በራሱ ግምትም ሆነ በእግዚአብሔር ፊት እየቀነሰ፣ እየወረደ የመጣ ይመስል ነበር። እርሱ ማለት ምንም እንዳልሆነ (ተራ ሰው እንደሆነ)፣ እግዚአብሔር ግን ሁሉም ነገር እንደሆነ በመሰለው ጊዜ፤ ራሱን በመካድ፣ አዳኙን እንደ ብቸኛ ጥንካሬውና ጽድቁ አድርጎ ሲይዝ፣ ያኔ መልሱ መጣ።”—The SDA Bible Commentary, vol. 2, p. 1035.

5. በጸሎት መጽናት ሐሙስ ፣ ጷጉሜ 05
ሀ. ሐዋርያት ስለ ጸሎት ምን ጠቃሚ ምክር ሰጥተዋል? 1ኛ ጴጥሮስ 4:7፤ ፊልጵስዩስ 4:6 “በጸሎት መትጋት በእጅጉ ያስፈልገናል። ይህንንም ከማድረግ ምንም ነገር አያደናቅፋችሁ። በነፍሳችሁና በየሱስ መካከል ክፍት የሆነ የግንኙነት መስመር ዘወትር እንዲኖር በማድረግ የሚገባችሁን ሁሉ አድርጉ። ጸሎት ወደ ሚደረግበት ስፍራ ለመሄድ እያንዳንዱን ዕድል ተጠቀመበት። ከእግዚአብሔር ጋር እውነተኛ ግንኙነት ማድረግ የሚፈልጉ ሁሉ ተግባራቸውን በታማኝት ለመፈጸምና ሊያገኙ የሚችሉትን ባርኮቶች በትጋትና በጉጉት ለመሰብሰብ ዝግጁዎች ሆነው በጸሎት ስብሰባዎች ላይ ይሳተፋሉ። የሰማይ ብርሃን ጨረር ሊያገኙ ወደሚችሉበት ስፍራ ራሳቸውን ለማስቀመጥ የሚረዳቸውን ዕድል ይጠቀመብታል።”—Steps to Christ, p. 98 ለ. እንደማንኛውም ወላጅ፣ ጌታ ልጆቹ ምን እንዲያደርጉ ይጠብቅባቸዋል? ሉቃስ 11:10፣ 13፤ ዮሐንስ 14:13፣ 14 “ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን በስሙ እንዲጸልዩ አዝዞአቸዋል። የክርስቶስ ተከታዮች በእግዚአብሔር ፊት የሚቆሙት በክርስቶስ ስም ነው። ለእነርሱ የተከፈለው መስዋዕት ከፍተኛ ዋጋ ያለው ስለሆነ የክርስቶስ ተከታዮች የሆኑ ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ ዋጋ ያላቸው ናቸው። የክርስቶስን ጽድቅ ስለያዙ የተከበሩ ናቸው። እግዚአብሔር የሚጠሩትን ሁሉ ስለ ክርስቶስ ይቅር ይላችዋል። በእርሱ በሚያምኑት ላይ የልጁን አምሳያ እንጂ የኃጢአተኛን አስከፊነት አያይም።”—The Desire of Ages, p. 667“ለእግዚአብሔር ልመናችንን ለማቅረብ የማንችልበት ጊዜ ወይም ቦታ የለም። በእውነተኛ ጸሎት ልባችንን እንዳናፈስ የሚከለክለን ምንም ነገር የለም። በመንገድ ላይ ከተሰበሰበ ህዝብ መኃል ሆነን፣ ወይም በስራ ተጠምደን ባለንበት ሁኔታም ቢሆን ነህምያ በንጉስ አርጤክሰስ ፊት መጠይቁን ሲያቀርብ እንዳደረገው፣ እኛም እግዚአብሔር መለኮታዊ ምሪት እንዲሰጠን ልንጠይቀው እንችላለን። በየትኛውም ቦታ ብንሆን በስውር የምንጸልይበትን ዕድል ልናገኝ እንችላለን።”—Steps to Christ, p. 99

የግል ክለሳና የመወያያ ጥያቄዎች አርብ ፣ መስከረም 01
1. ለሁሉም አማኞች በጸሎት ውስጥ የመጽናት ምሳሌ የተሰጠው ምንድን ነው? 2. በየማለዳ የጸሎትን አስፈላጊነት የሚያሳየው የትኛው ትንቢት ነው? 3. ለተሳካ ጸሎት ቅድመ ሁኔታ ምንድን ነው? 4. መልስ እየጠበቅን መጸለያችን መቀጠል ያለብን ለምንድነው? 5. በየሱስ ስም መጸለይ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ግለጽ።
 <<    >>