ከየሱስ ጋር መራመድ << >> ሰንበት፣ ነሐሴ 23፣ 2018 9ኛ ትምህርት ሥራ እና ሕይወት የመታሰቢያ ጥቅስ፡- “ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው።“ (ዮሐንስ 1፡12)። ለንባብ የተመረጠው መጽሐፍ ፡ Steps to Christ, chapter 9፣ pp. 77–83። “የክርስቶስ ራስን መስዋት አድርጎ የመስጠት የፍቅር መንፈስ፣ የሰማይን መንግሥት ያጥለቀለቀ መንፈስ ሲሆን እውነተኛ ደስታን ለማግኘትም በጣም አስፈላጊ ነገር ነው። የክርስቶስ ተከታዮችም ተመሳሳይ መንፈስን በመጋራት፣ ተመሳሳይ ሥራን ይስራሉ።”—Steps to Christ, p. 77። 1. ሕይወትና ብርሃን እሁድ ፣ ነሐሴ 17 ሀ. በተፈጥሯዊው ሰበዓዊ ልብ ችላ የተባለው ምንድን ነው - እና ውጤቱስ ምን ይሆናል? ዮሐንስ 1:4፣ 5። “እግዚአብሔር ለዓለማት ሁሉ የሕይወት፣ የብርሃንና የደስታ ምንጭ ነው። የብርሃን ጨረር ከጸሐይ እንደሚፈነጥቅ፣ የወንዝ ውሃም ከምንጭ ፈልቆ እንደሚጐርፍ እግዚአብሔርም በረከቱን ለፍጥረቱ ሁሉ አብዝቶ ይሰጣል። መለኮታዊ ሕይወት በአንድ ሰው ልብ ውስጥ ሲኖር ከዚያ ሰው ልብ ለሌሎች ሰዎች የሚሆን ፍቅርና በረከት ይፈልቃሉ።”—Steps to Christ, p. 77። ለ. የክርስቶስ ፍቅር በልብ ውስጥ ሲከበር፣ በህይወት ውስጥ ምን ይታያል? 2ኛ ቆሮንቶስ 2:14፣ 15፤ 5:14። “የክርስቶስ ፍቅር በአንድ ሰው ልብ ውስጥ ሲኖር ልክ ጣፋጭ ማዕዛ እንዳለው እጣን ሊሸሸግ አይችልም። የዚህን ፍቅር ቅዱስ ኃይል የምናገኛቸው ሰዎች ሁሉ ያዩታል (ይሰማቸዋል)። በአንድ ሰው ልብ ውስጥ የሚኖረው የክርስቶስ መንፈስ የደረቀውን ሁሉ እንደሚያረሰርስ፣ ሊሞቱ የቀረቡትንም በፍጥነት ወደ ሕይወት ውሀ እንዲመጡ እንደሚያደርግ በበረሀ ውስጥ እንዳለ የውሀ ምንጭ ነው።”—Ibid.“የግል ፍላጐታችንን ብቻ የምናሳድድ ሳንሆን ሌሎችም እኛ ያገኘነውን ዕድልና በረከት እንዲያገኙ የምንፈልግ መሆናችንንም ዓለም ሊያውቅ ይገባዋል። ኃይማኖታችን የማናዝንና ግንትሮች እንዳላደረገን ዓለም ይወቅ። ክርስቶስን አግኝተናል የሚሉ ሁሉ እርሱ ሰዎችን ለመጥቀም የሰጠውን ዓይነት አገልግሎት መስጠት አለባቸው። ክርስቲያኖች ፊታቸውን አጥቁረው የሚኖሩና የከፋቸው ናቸው ብለው ሰዎች የተሳሳተ አስተሳሰብ እንዲኖራቸው ማድረግ የለብንም። ዓይኖቻችን በክርስቶስ ላይ ካተኮሩ ቸር አዳኝ መሆኑን እናያለን፡፡ ከፊቱም ብርሃን እንወስዳለን። መንፈሱ በሚገዛበት ቦታ ሁሉ ሰላም ይገኛል። በእግዚአብሔር የሰከነና የተቀደሰ እምነት ስለሚኖረን ከዚያ ደስታ ይኖራል።”—The Desire of Ages, p. 152. 2. የጸጋ ተካፋዮች ሰኞ ፣ ነሐሴ 18 ሀ. የሱስን እንደ አዳኛችን ስንቀበል፣ ምን ዓይነት ፍላጎታችን ይሟላል? ዮሐንስ 1:12፣ 13፤ 1ኛ ቆሮንቶስ 1:4፣ 5፤ ሮሜ 5:1፣ 2 “የክርስቶስ ጸጋ ተካፋዮች የሆኑ ሁሉ ይህንን የሰማይ ስጦታ ሌሎች ክርስቶስ የሞተላቸው ሰዎችም እንዲያገኙ ማንኛውንም አገልግሎትና መስዋዕትነት ለመክፈል የተዘጋጁ ይሆናሉ። በዓለማችን ላይ የተሻለ ሕይወት እንዲኖር የሚቻላቸውን ሁሉ ያደርጋሉ። እንደዚህ ያለ መንፈስ ከልብ ወደ ጌታዋ የተመለሰች ነፍስ ፍሬ ነው። አንድ ሰው በእርግጥ ወደ ክርስቶስ ለመመለሱ ማረጋገጫው፤ እርሱ ስላገኘው የከበረ ወዳጅ ስለ የሱስ ለሌሎች ለመመስከር ፍላጎት ሲያድርበት ነው። ይህንን የሚያድንና የሚቀድስ እውነት ለራሱ ብቻ ይዞ መቀመጥ አይችልም። የክርስቶስን ጽድቅ ከለበስንና በልባችን በሚኖረው የመንፈሱ ደስታ ከተሞላን ዝም ልንል አንችልም። ጌታ ቸር እንደሆነ ከቀመስንና ካየን የምንናገረው ነገር ይኖረናል። እንደ ፊሊጶስ እኛም መድኅንን ካገኘን በኋላ ሌሎችን ወደ እርሱ እንጋብዛለን።”—Steps to Christ, p. 78. ለ. ችግሮችና ፈተናዎች ሲያጋጥሙን የሐዋርያው ጳውሎስ ምክር ምንድን ነው? ዕብራውያን 4:16። “የሱስ ለልጆቹ የሚያስፈልጋቸውን ያውቃል፣ ጸሎታቸውንም ሊያዳምጥ ይወዳል። ልጆቹ ዓለምንና ሀሳባቸውን ከእግዚአብሔር ላይ እንዲያነሱ የሚያደርጋቸውን ነገር ሁሉ ይከልክሉ፣ ከዚያም የእግዚአብሔር ዓይን ውስጣዊ ልባቸውን ይመለከት ዘንድ ከእግዚአብሔር ጋር ብቻቸውን መሆናቸው ይሰማቸው፣ በዚያን ጊዜ እሱ የነፍሳቸውን ፍላጎት ያነባል እንዲሁም ከእነሱም ጋር ይነጋገራል።”—Sons and Daughters of God, p. 121. ሐ. እግዚአብሔር ልጅ ከሆንን በኋላ ለሌሎች ምን ዕዳ አለብን? ሮሜ 1:14፣ 15. “ጳውሎስ በምን ሁኔታ ነበር ለአይሁዳዊም ሆነ ለግሪክ ሰው ባለዕዳ የነበረው? ለእያንዳንዱ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር እንደተሰጠው ሁሉ፣ ‘እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ አስተምሩ፣ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፣ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው፤ እነሆም፣ እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ’’ የሚለው ተልዕኮ ለእርሱም ተሰጥቶታል፡፡ ጳውሎስ ክርስቶስን በመቀበል ይህን ተልእኮም ተቀበለ። ለሁሉም የሰው ልጆች ማለትም ለአይሁድና ለአሕዛብ፣ ለተማሩትና ላልተማሩ፣ ከፍተኛ ሥልጣን ላላቸውና በጣም ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙት ሁሉ የመሥራት ግዴታ በእሱ ላይ እንደወደቀበት ተገነዘበ።”—The SDA Bible Commentary [E. G. White Comments], vol. 6, p. 1067። 3. የመለወጥ ፍሬ ማክሰኞ ፣ ነሐሴ 19 ሀ. መንፈስ ቅዱስ በልባችን ውስጥ ከኖረ፣ በመጀመሪያ ከምናደርጋቸው ድርጊቶቻችን አንዱ ምን ይሆናል? ዮሐንስ 1:41፣ 42. “ስለ ክርስቶስ የማዳን ኃይል (ስለ ፍቅሩ ማራኪነት) እንዲሁም አሁን በዓይን ስለማይታየው ነገር ግን ስለሚመጣው የጌታ መንግስት እውነታ ለእነርሱ ለመንገር እንጓጓለን። የሱስ የሄደበትን ፍለጋ ለመከተል ጥልቅ ፍላጎት ያድርብናል። በዙሪያችን ያሉት ሰዎችም «የዓለምን ኃጢአት ሁሉ የሚያስወግደውን የእግዚአብሔርን በግ» (ዮሐ. 1: 29) እንዲመለከቱ የጋለ መሻት ይኖረናል።“ሌሎች ሰዎች እንዲባረኩ የምናደርገው ጥረት በራሳችን ላይ በረከት ያመጣልናል። በድነት ስራ ላይ እንድንተባበር እግዚአብሔር ሲጋብዘን ዓላማው ይህ ነበር። በፀጋው የመለኮታዊው ኃይል ተካፋዮች እንድንሆን አድርጎናል፤ በምላሹም እኛ የተስጠንን በረከት ለሌሎች ሰዎች እንድናካፍል ይፈልጋል። እግዚአብሔር ይህንን በረከት ለሰዎች መስጠቱ ትልቅ ደስታና ክብር ነው። በፍቅር አገልግሎት ውስጥ የሚሳተፉ ሁሉ ወደ ፈጣሪያቸው ይበልጥ እየተጠጉ ይመጣሉ።”“ወንጌልን የማሰራጨት ኃላፊነትንና የፍቅር አገልግሎት ማበርከትን እግዚአብሔር ለመላእክቱ መስጠት ይችል ነበር። ዓላማውን ለማከናወን ሌላ መንገድ መቀየስም ይችል ነበር። ቢሆንም ከታላቅ ፍቅሩ የተነሳ ከእርሱ፣ ከክርስቶስና ከመላእክቱ ጋር ተባብረን በመስራት በዚያ ውስጥ የሚገኘውን በረከት፤ ደስታ እና መንፈሳዊ እርካታ እንድንካፈል ፈለገ።”“የክርስቶስ መከራ ተካፋዮች ስንሆን የእርሱን ርህራኄ ጭምር እንጋራለን። ራስን መስዋዕት በማድረግ የሚከናወን እያንዳንዱ በጎ አድራጎት፣ በድርጊት ፈጻሚው ልብ ውስጥ የለጋስነትን ስሜት የሚያጠናክር ሲሆን «በእርሱ ድህነት ባለ ጠጎች ትሆኑ ዘንድ ስለ እናንተ ድሀ» (2ኛ ቆሮ. 8: 9) ከሆነው የዓለም አዳኝ ጋር ይበልጥ ያቀራርበዋል። በመሆኑም አምላክ ለእኛ ያለውን ዓላማ በእርግጠኝነት ስንከተል ሕይወታችን ለሌሎች በረከት ይሆናል።”—Steps to Christ, pp. 78–80። ለ. ከዘመዶችና ከጎረቤቶች ጋር ባለን ግንኙነት የትኛው የክርስቶስ ምሳሌ ሊመራን ይገባል? ገላትያ 6:9፣ 10፤ ዮሐንስ 9:4። “ክርስቶስ ለደቀመዛሙርቱ በነደፈው እቅድ መሠረት ብትሰሩና ነፍሳትን ወደ እርሱ ብትማርኩ፣ መለኮታዊውን ነገር በጥልቀት ለመለማመድና ጠንቅቆ ለማወቅ የሚኖራችሁ ፍላጎት ይጨምራል፤ ጽድቅንም የምትራቡና የምትጠሙ ትሆናላችሁ። እግዚአብሔርን የሙጥኝ ትላላችሁ ፤ እምነታችሁም ይጠነክራል፣ ነፍሳችሁም ከድነት የውሃ ጉድጓድ ጠለቅ አድርጋ መቅዳትና መጠጣት ትችላለች። ተቃውሞዎችን እና ፈተናዎችን መጋፈጥ ወደ መጽሐፍ ቅዱስ እና ወደ ጸሎት ይመራችኋል። በጸጋ እና በክርስቶስ እውቀት ታድጋላችሁ፣ በዚህም የበለፀገ ተሞክሮ ታዳብራላችሁ።”—ibid, p. 80። 4. ራስ ወዳድነት የሌለበት ሥራ ረቡዕ ፣ ነሐሴ 20 ሀ. ዛሬ እንደ ቤተ ክርስቲያን አባላት የተጋረጠብንን አንድ ትልቅ አደጋ ጥቀሱ። ሚልክያስ 3:8-10 ። “በአሁኑ ጊዜ [የሰንበት ጠባቂ አድቬንቲስቶች] ትልቁ አደጋ የንብረታቸው ክምችት ነው። አንዳንዶች ጭንቀታቸውንና ድካማቸውን ያለማቋረጥ እየጨመሩ ናቸው፤ ከመጠን በላይ በራሳቸው ላይ ጫና እያደረጉ ነው። ውጤቱም እግዚአብሔርንና የእርሱን ዓላማ ሊረሱ ተቃርበዋል፤ በመንፈሳዊነትም ሞተዋል። ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል፣ ሥጦታ ማምጣት። መሥዋዕት (ሥጦታ) እየጨመረ አይደለም፣ ይልቁንስ እየቀነሰ እና እየጠፋ ነው። . . . በህዝባችን መካከል ያለው አብዛኛው ሀብት፣ በሐብቱ ባለቤቶች ላይ ጉዳት ብቻ ያስከተለ መሆኑ በተግባር ተረጋግጦአል፡፡”—Testimonies for the Church, vol. 1, p. 492. ለ. አማኞች በጌታ በየሱስ ክርስቶስ ጸጋና እውቀት እንዲዳብሩ የሚያግዙት የትኞቹ ክርስቲያናዊ በጎ ተግባራቶች ናቸው? 1ኛ ጴጥሮስ 4:8-10 ፤ ዕብራውያን 13:2። “ለአብርሃምና ለሎጥ የተሰጠው ልዩ ዕድል ለእኛ አልተከለከለም። የእግዚአብሔርን ልጆች በመልካም እንግድነት በመቀበል፣ አንድ ቀን እኛም የእርሱን መላእክት በመኖሪያችን ልንቀበል እንችላለን። በእኛም ዘመን ቢሆን፣ መላእክት በሰው መልክ ወደ ሰዎች ቤት በመግባት በጥሩ መስተንግዶ ከእነርሱ ጋር ደስ ይሰኛሉ። እንዲሁም በእግዚአብሔር መገኘት ብርሃን የሚኖሩ ክርስቲያኖችም ሁልጊዜም በማይታዩ መላእክት ይታጀባሉ ፤ እናም እነዚህ ቅዱሳን ፍጥረታት ከቤታችን ሲወጡ በረከትን አስቀምጠው ያልፋሉ።”—ibid, vol. 6፣ p. 342። ሐ. ዛሬ በአማኞች መሟላት ያለበት ምን ዓይነት ፍላጎት ነው? 2ኛ ቆሮንቶስ 10:16። “የቤተክርስቲያኖቻችን ምዕመናን እስካሁን ድረስ ገና በጥቂቱ የጀመሩትን ሥራ አሁን በኃይል ማከናወን ይችላሉ። ማንም ሰው ለዓለማዊ ጥቅም ብቻ ወደ አዳዲስ ቦታዎች መሄድ የለበትም፤ ነገር ግን የኑሮ መተዳደሪያ ለማግኘት ምቹ ቦታ ሲገኝ፣ በሚገባ በእውነት ላይ የተመሠረቱ አንድ ወይም ሁለት ቤተሰቦች፣ በአንድነት ሆነው በሚስዮናዊነት እንዲሠሩ ይደረጉ። ለነፍሳት የፍቅር ስሜት ሊሰማቸው፣ እነሱን ለማገልገልም ሸክም ሊሰማቸው ይገባል፣ እንዲሁም እነዚህን ነፍሳት ወደ እውነት እንዴት ማምጣት እንደሚችሉ ጥናት ማድረግ አለባቸው። ጽሑፎቻችንን ማሰራጨት፣ በቤታቸው ስብሰባዎችን ማድረግ፣ ከጎረቤቶቻቸው ጋር መተዋወቅ እና ወደ እነዚህ ስብሰባዎች እንዲመጡ መጋበዝ ይችላሉ። በዚህም ብርሃናቸው በመልካም ሥራዎቻቸው እንዲበራ ማድረግ ይችላሉ።”—ibid, vol 8፣ p. 245።“እያንዳንዱ ሰው እንደ ችሎታው ለእርሱ ይሰራ ዘንድ፣ የአገልግሎት መንፈስ መላውን ቤተክርስቲያን እንዲቆጣጠር እግዚአብሔር ለረጅም ጊዜ ሲጠባበቅ ቆይቷል። የተሰጠውን የወንጌል ተልእኮን ለመፈፀም፣ የእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን አባላት የተሰጣቸውን ሥራ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር ባሉ ቦታዎች ሲያከናውኑ፣ በቅርቡ መላው ዓለም በሙሉ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፤ ጌታ የሱስም በኃይልና በታላቅ ክብር ወደዚህች ምድር ይመለሳል።”—The Acts of the Apostles, pp. 111 5. ታማኝ ተወካዮች ሐሙስ ፣ ነሐሴ 21 ሀ. የወንጌል አደራ ከተሰጣቸው ሁሉ - በተለይም ከሠራተኞች - ምን ይጠበቃል? 1ኛ ቆሮንቶስ 4:1፣ 2፤ ራእይ 2:10። “ስለሚመጣው አደጋ ኃጢአተኞችን በማስጠንቀቅ ከአደጋ ማምለጥ ወደሚችሉበት አስተማማኝ ሥፍራ ይመሯቸው ዘንድ፣ ጌታ በእነሱ በኩል ሥራውን መሥራት እንዲችል ወደ እግዚአብሔር እጅግ ቅርብ ሆኖ መኖር እና የመንፈሱን መፍሰስ በሙላት ማግኘት በጽዮን ቅጥር ለቆሙ ጠባቂዎች መብታቸው (ልዩ መታደል) ነው። በእግዚአብሔር ተመርጠው በቅዱስ (በኪዳኑ) ደም ታትመው፣ ከሚመጣው ጥፋት ወንዶችንና ሴቶችን መታደግ ይኖርባቸዋል። በታማኝነት ባልንጀሮቻቸውን [የአምላክህን ትዕዛዛት] የመተላለፍን (የኃጢአትን) የማይቀረውን እርግጠኛ ውጤት [ሞት] ማስጠንቀቅ እና የቤተክርስቲያንን ጥቅም በታማኝነት መጠበቅ አለባቸው።”—Gospel Workers, pp. 15። ለ. ዳንኤል ለዚህ ዘመን ወጣቶች ምን ምሳሌ ትቷል (አስቀምጧል) ? ዳንኤል 1:8፣ 15። “ እግዚአብሔር ከዳንኤል ተሞክሮ ትምህርት እንድንማር ይፈልጋል። ድልነሽትን ለመቀዳጀት፣ በጥረታቸውና በድካማቸው ብርታትና ቅልጥፍናን ለማግኘት፣ ለጸጋው በእግዚአብሔር ላይ ቢተማመኑ ልክ እንደዚህ ዕብራዊ ኃያላን ሊሆኑ የሚችሉ ብዙ ሰዎች አሉ። ዳንኤል ለሽማግሌዎችም ሆነ ለወጣቶች ፍጹም የሆነ ጨዋነትን አሳይቷል። ለእግዚአብሔር ምስክር ሆኖ በመቆም፣ ሰማይ ቃሉን ቢሰማ ወይም ሥራውን ቢያይ የማያፍርበት ይሆን ዘንድ፣ እንዲህ ያለውን መንገድ ለመከተል ፈለገ። ዳንኤል ከንጉሡ ማዕድ የቀረበውን የቅንጦት ምግብ እንዲበላ ሲጠየቅ፣ በፍላጎት አልነሆለለም ፤ እንደፈለገውም ለመብላትና ለመጠጣት መሻቱን አልገለጸም። አንድም የተቃውሞ ቃል ሳይናገር ጉዳዩን ወደ እግዚአብሔር ወሰደው (አቀረበው)። እሱና ጓደኞቹ ከእግዚአብሔር ጥበብን ፈለጉ ፤ እናም ልባዊ ጸሎታቸውን ጨርሰው ሲወጡ ውሳኔያቸውን አደረጉ። ዳንኤል በእውነተኛ ድፍረትና ክርስቲያናዊ ጨዋነት ጉዳዩን ለተሾመላቸው አለቃ አቀረበው፣ ቀላል ያለ አመጋገብ እንዲፈቀድላቸው ጠየቀ። እነዚህ ወጣቶች የኃይማኖት መርሆቻቸው አደጋ ላይ እንደወደቀ ተሰማቸው፣ እናም ለእርዳታ በሚወዱትና በሚያገለግሉት በእግዚአብሔር ላይ ተደገፉ።”—Testimonies to Ministers, p. 263. የግል ክለሳና የመወያያ ጥያቄዎች አርብ ፣ ነሐሴ 22 1. እግዚአብሔር ብርሃንን ወደ ዓለም ውስጥ እንዲያስገባ ያስፈለገው ምን ዓይነት የዓለም ሁኔታ ነው? 2. በአማኞች ሕይወት ውስጥ ምን አስደናቂ ለውጥ ይታያል? 3. በረከትን ስንቀበል ምን ምላሽ መስጠት አለብን? 4. እያንዳንዳችን ሌሎችን ማገልገል የምንችልባቸውን አንዳንድ መንገዶች ግለጽ። 5. የዳንኤል ታማኝነት ለእኔ መነሳሻ የሚሆነው እንዴት ነው? << >>