ከየሱስ ጋር መራመድ << >> ሰንበት፣ መስከረም 16፣ 2018 13ኛ ትምህርት በጌታ መደሰት የመታሰቢያ ጥቅስ፡- “ነገር ግን ክብሩ ሲገለጥ ደግሞ ሐሤት እያደረጋችሁ ደስ እንዲላችሁ፥ በክርስቶስ መከራ በምትካፈሉበት ልክ ደስ ይበላችሁ።” (1ኛ ጴጥሮስ 4፡13) ለንባብ የተመረጠው መጽሐፍ ፡ Steps to Christ, chapter 13፣ pp. 115–126. “ጌታ ወንዶችና ሴቶች ልጆቹን ደስተኛ፣ ሰላም የሞላቸው እና ታዛዥ እንዲሆኑለት ይፈልጋል።”—Steps to Christ, p. 124. 1. ብርሃን ተሸካሚዎች እሁድ ፣ መስከረም 10 ሀ. የሱስ በዚህ ዓለም ውስጥ ደቀ መዛሙርቱ ምን ኃላፊነት እንዳለባቸው ተናግሯል? ማቴዎስ 5: 13-16። “ክርስቲያኖች ለመንግስተ ሰማይ መንገድ ብርሃን አብሪዎች ናቸው። ከክርስቶስ የሚመነጨውና በእነርሱ ላይ የሚያበራው ብርሃን አንፀባራቂዎች ናቸው። ሕይወታቸውና ባሕርያቸው ለሌሎች ስለክርስቶስና አገልግሎቱ ትክክለኛን አመለካከት የሚያስጨብጡ ሊሆኑ ይገባል።”—Steps to Christ, p. 115 ለ. አማኞች ለሁሉም ሰዎች ምን መሆን አለባቸው? ዮሐንስ 17:18፣ 23፤ 2ኛ ቆሮንቶስ 5:20። “የሱስ በእያንዳንዱ ልጁ በኩል ወደ ዓለም ደብዳቤ ልኳል፡፡ እናንተ የክርስቶስ ተከታዮች ከሆናችሁ በእናንተ ወደ የቤተሰቦቻችሁ፣ መንደሮቻችሁ፤ ጎዳናዎች እና የምትኖሩበት ቦታ ሁሉ ደብዳቤ ልኳል ማለት ነው። በእናንተ የሚኖረው የሱስ ከእርሱ ጋር ላልተዋወቁ ሰዎች ልብ በአኗኗራችሁ በኩል መናገር ይፈልጋል። ምንአልባትም እነዚህ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን አላነበቡም ይሆናል ወይም አንብበውትም እንኳን በየገፁ ለልባቸው የሚጮኸውን ድምፅ አልሰሙም ይሆናል፤ የእግዚአብሔርን ፍቅር በስራው አላዩትም ይሆናል። እናንተ ግን የየሱስ እውነተኛ ወኪል ከሆናችሁ እነዚህ ሰዎች የእርሱን በጎነት በእናንተ በኩል በመረዳት ለፍቅሩና ለአገልግሎቱ እጃቸውን ይሰጣሉ።”—Ibid. ሐ. ይህንን ተልዕኮ መፈጸም የሚቻለው እንዴት ብቻ ነው? 2ኛ ቆሮንቶስ 3፡2–5። 2. እግዚአብሔር ቸርነት ሰኞ ፣ መስከረም 11 ሀ. እግዚአብሔር ለልጆቹ ያለው ከፍተኛው የፍቅር መግለጫ ምንድን ነው? ዮሐንስ 3:16፤ ሮሜ 5: 6-10 “ የእግዚአብሔርን ፍቅር ስንጠራጠርና ቃል ኪዳኑን ሳናምን ስንቀር እርሱን እናዋርደዋለን፤ ቅዱስ መንፈሱን እናሳዝናለን። ሕይወቷን በሙሉ የልጆችዋን ፍላጎት ለማሟላትና ለእነርሱ ምቾት ለሰዋች አንዲት እናት፤ ልጆቿ ያደረገችውን ነገር ሁሉ ከምንም ሳይቆጥሩ ያለማቋረጥ ቢያማርሯት ምን ይሰማታል? ፍቅሯን ተጠራጠሩት እንበል ፤ ይህ ታዲያ መንፈሷን አይሰብረውምን? ልጆቹ ለአባታቸው ያለው ምላሽ እንደዚህ ከሆነ የአባታቸው ስሜት ምን አይነት ይሆን? ታዲያ ሰማያዊ አባታችን እኛ ሕይወት እንዲኖረን አንድያ ልጁን እስኪሰጠን ድረስ ያስገደደውን ፍቅሩን ስናጣጥል ምን ይሰማው ይሆን? ሐዋርያው በሮሜ 8:32 ላይ «ለገዛ ልጁ ያልራራለት ነገር ግን ስለሁላችን አሳልፎ የሰጠው ከክርስቶስ ጋር ደግሞ ሁሉንም ነገር እንዲያው እንዴት አይሰጠንም!» ሲል ጽፏል። ይህ የተስፋ ቃል ቢሰጣቸውም ስንቶች ናቸው በድርጊታቸው አልፎም በቃላቸው «ለእኔ ጌታ እንዲህ አይደለም። ምናልባት ሌሎችን ይወድ ይሆናል። እኔን ግን አይወደኝም።» የሚሉ?”—Steps to Christ, p. 118, 119. ለ. እግዚአብሔር ለልጆቹ ሁሉንም ነገር መስጠት እንደሚፈልግ የሚያረጋግጠው ምንድን ነው? ሮሜ 8:32 “እናንተ እጅግ ዋጋ ቢስ እንደሆናችሁ የሚሰማቸው፣ ጉዳያችሁን በሙሉ ለእግዚአብሔር አደራ ለመስጠት አትፍሩ። ስለ ዓለም ኃጢአት ራሱን በክርስቶስ አሳልፎ በሰጠ ጊዜ፣ የእያንዳንዱን ነፍስ ጉዳይ በራሱ ወሰደ (ተሸከመ)። ‘ለገዛ ልጁ ያልራራለት ነገር ግን ስለ እኛ አሳልፎ የሰጠው ያው ከእርሱ ጋር ደግሞ ሁሉን ነገር እንዲያው (በነፃ) እንዴት አይሰጠንም?’ ሮሜ 8፡32። ታዲያ ለእኛው መጽናናትና ብርታት ይሆን ዘንድ የሰጠንን በቸርነት የተሞላውን ይህን ቃል አይፈጽመውምን?“ክርስቶስ ርስቱን ከሰይጣን አገዛዝ የመዋጀትን ያህል የሚፈልገው ሌላ ምንም ነገር የለም።”—Christ’s Object Lessons, p 174. ሐ. ይህ ፍቅር በእኛ ህይወት እንዴት ሊንጸባረቅ ይችላል? 1ኛ ዮሐንስ 4:9-12 “በሥራቸው፣ የተሳካላቸው ክርስቲያን ሠራተኞች ክርስቶስን ማወቅ አለባቸው፤ እሱንም ለማወቅ ፍቅሩን ማወቅ አለባቸው። በሰማይ የሠራተኛነታቸው ብቃት የሚለካው ክርስቶስ እንደወደደ በመውደድ እና እሱ እንደሠራ በመሥራት ችሎታቸው ነው።”“በተግባርና በእውነት እንጂ፤ በቃል ብቻ አንዋደድ” ሲል ሐዋርያው ጽፏል። የክርስቲያን ባሕርይ ሙላት (ፍጽምና) የሚገኘው ሌሎችን ለመርዳትና ለመባረክ ያለን ፍላጎት ከውስጥ ያለማቋረጥ ሲወጣ ነው። የአማኙን ነፍስ የሚከበበው የዚህ ፍቅር ድባብ ለሕይወት የሕይወት ጣዕም እንዲኖረውና እግዚአብሔርም ሥራውን እንዲባርክ ያስችለዋል።”—The Acts of the Apostles, pp. 551. 3. የክርስቶስ ፈተናዎች ማክሰኞ ፣ መስከረም 12 ሀ. ለሰዎች መዳን ባከናወነው ሥራ የክርስቶስን ሕይወት ምን ባህርይ ይገልፀዋል (በምን ተለይቶ ይታወቃል)? ኢሳይያስ 53:10፣ 7 “[የክርስቶስ] ሕይወት የማያቋርጥ የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ ሕይወት ነበር። እንደ መንገደኛ ቆጥረው ወዳጆቹ ከሚያስተናግዱት በስተቀር በዚህ ዓለም ውስጥ ምንም ቤት አልነበረውም። በመካከላችን የድሆችን ሕይወት ለመኖር፣ በችግረኞችና በስቃይ ውስጥ በሚገኙት መካከል ለመራመድና ለመሥራት መጣ፡፡ ሳይታወቅና ሳይከበር፣ ብዙ ነገር ባደረገላቸው ሰዎች መካከል ተመላለሰ።”—Gospel Workers, pp. 42፣ 43።“[የእግዚአብሔር ልጅ] እግሮቹ የሚያመሩት ወደየት እንደሆነ ጠንቅቆ ቢያውቅም፣ ወደ ሞት እንደሚያመራ ቢገባውም፣ የሚያወርደው እንባ ግን ለራሱ አልነበረም። በፍጥነት እየደረሰ ያለው፣ የሰቆቃው ምድረ-ትዕይንት የሆነው ጌቴሰማኒ በፊቱ ነበር። “ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት” [ኢሳ 53÷7] የሚሆንበት፣ ለእርሱም በቅርብ የሚከፈተው፣ ለብዙ መቶ ዓመታት በመስዋዕትነት ይታረዱ ዘንድ የሚነዱበት የበጎች በርም እይታው ውስጥ ነበር። የስቅላት ቦታው ቀራንዮም ከዚያ ሩቅ አልነበረም። በቅርቡ ክርስቶስ በሚራመድበት መንገድ ላይ ታላቅ የሰቆቃ ጽልመት ይወድቃል፤ ነፍሱን ስለ ኃጢአት ይሰጣልና። ሆኖም በዚህ የደስታ ሰዓት የኃዘን ጥላ የጣለበት እነዚህን በርሱ ላይ የሚመጡትን ትእይንቶች ማሰላሰሉ አልነበረም። ሰው ከሚችለው በላይ የሆነው ስቃዩ በውል ቢገባውም ቅሉ ያንን ራስ ወዳድነት የሌለበትን መንፈሱን ግን አላደበዘዘበትም ነበር። የሚያለቅሰው፣ ሊያድናቸውና ሊባርካቸው ለመጣላቸው፣ በእውርነታቸውና ንሰሐ መግባትን እምቢ በማለታቸው ምክንያት ለሚጠፉት በሺዎች ለሚቆጠሩ የሩሳሌማውያን ነበር።”—The Great Controversy, p. 18። ለ. በመከራውና በፈተናው ወቅት፣ ሥራውን ለማጠናቀቅ ለየሱስ ድፍረት የሰጠው ምንድን ነው? ኢሳይያስ 53:11፤ ዕብራውያን 12:2። “ከጨለማ ኃይላት ጋር ያደረገው የአዳኙ ጦርነት ውጤት ለዳኑት የዘላለም ደስታ፣ ለእግዚአብሔር ክብር የሚጨምር ነው። አባት በተከፈለው ዋጋ የረካበት የነፍስ ዋጋ ግምት ይህንን ያህል ነው፤ የታላቁን መስዋዕትነቱን ፍሬዎች በማየት ክርስቶስ ራሱ ይረካል።”—Ibid., p. 652.“ብዙ ጊዜ የሱስ እንዳነባ ሲጠቀስ እንደሳቀ ፈፅሞ አይታወቅም። እርግጥ ነው አዳኛችን ልቡ በሀዘን ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች ሁሉ የተከፈተ በመሆኑ የሕማም ሰው ነበር እንደዚሁም ሐዘን ይገባዋል። ምንም እንኳ ሕይወቱ ራስን በመካድ፣ በህመም እና ጥንቃቄ የተሞላ ቢሆንም መንፈስ ሰባራ ግን አልነበርም። ገፅታው የሀዘንና የጉስቁልና አልነበረም። ነገር ግን የሰላም ድባብ ሸፍኖት ነበር። እርሱ መልካም የሕይወት ምንጭ ነበር። በሄደበት ሁሉ ሰላም፣ ዕረፍት፤ ደስታና እርካታ ይዞ ይሄድ ነበር።”—Steps to Christ, p. 120 4. በፈተናዎች መካከል መደሰት ረቡዕ ፣ መስከረም 13 ሀ. አማኙን ፈተና ሲገጥመው፣ በዚህ መንፈሳዊ ጦርነት አሸናፊነትን እንዲቀዳጅ ምን ይደረግለታል? ኤፌሶን 6: 11-18። “ሁሉም ሰው ይፈተናል። እያንዳንዱ ሰው ሊሸከመው ከባድ የሆነበት ሀዘን፣ ሊቋቋመው በብርቱ የበዛበት ፈተና አለበት። የሚያስጨንቋችሁን ነገሮች እንደ እናንተ ጠፊ ለሆኑት ሰዎች አትንገሩ። ይልቁንም በፀሎት ሁሉንም ነገር ወደ እግዚአብሔር አምጡት። ከአፋችሁ የጥርጣሬ እና የተስፋ መቁረጥ ቃል እንዳይወጣ የራሳችሁ ሕግ አድርጉት። ይህን በማድረጋችሁና በተስፋ ቃል እንዲሁም በተቀደስ ፈገግታ የሌሎችን ሕይወት ብሩህ ልታደርጉ እንዲሁም በሕይወት ተግዳሮት ላይ ላለባቸው ትግል ጥንካሬ ልትሆኗቸው ትችላላችሁ።”—Steps to Christ, p. 119፣ 120. ለ. ብዙዎች ሲፈተኑና ሲቸገሩ በእምነትና በጥርጣሬ መካከል ለምን ይዋለላሉ? ምንስ ማድረግ አለባቸው? ማቴዎስ 14:28 - 31፤ ያዕቆብ 1:2። “የብዙ ሰዎች ነፍስ ከራሳቸው ጋር በሚያደርጉት ግጭት እና ከኃጢአት ኃይል የተነሳ ፈጽሞ ለመውደቅ እየተፍገመገመች በአደገኛ ሁኔታ በፈተና ውስጥ አለች። እንዲህ ዓይነቱ ሰው በሚያደርገው ግብግብ ተስፋ አታስቆርጡት። በማበረታቻና እርሱን በመንገዱ ሊያነቃቁት በሚችሉ በተስፋ ቃላት አስደስቱት። በዚህም የክርስቶስ ብርሃን በእናንተ ያብረቀርቃል «ለራሳችን አንኖርም» (ሮሜ 14:7)። ሳታውቁት በምታደርጉት ነገር ሌሎች ሊበረታቱ እና ሊጠነክሩ ወይም ተስፋ ሊቆርጡ እንዲሁም ከክርስቶስ እና ከእውነት ሊርቁ ይችላሉ።”“ስለክርስቶስ ባህርይ እና ሕይወት ብዙዎች የተሳሳተ አስተሳሰብ አላቸው። እነዚህ ሰዎች፥ ክርስቶስ የደስታ ጸዳል የሌለው፣ ወና፣ ባዶ፣ ጎስቋላና ደስታ የራቀው እንደሆነ አድርገው ያስቡታል። በብዙ ሁኔታ፤ ሁሉም ሃይማኖቶች ማለት ይቻላል፤ የክርስቶስን የምድር ሕይወት በዚህ ዓይነት ጭጋጋማ ዕይታ ያዩታል።”— ibid, p 120. ሐ. የጻድቃን መንገድ በፈተና መካከል እንኳን እንዴት ብሩህ ነው? ምሳሌ 4:18፤ ፊልጵስዩስ 4:4። “መንገዱ አስቸጋሪና አቀበት የበዛበት ሊሆን ይችላል፤ በቀኝና በግራ ወጥመዶች ሊኖሩ ይችላሉ፤ በጉዟችን ድካምን መቋቋም ሊኖርብን ይችላል፤ ስንደክም፣ እረፍት ሲናፈቀን፣ አሁንም ጉዞአችንን መቀጠል ይኖርብን ይሆናል፤ ድካም ሲያጠቃን፣ ውጊያችንን መፋለም ይኖርብናል፤ ተስፋ በሚያስቆርጥ ሁኔታም ብንሆን ተስፋ ማድረግ አለብን፤ ዳሩ ግን ክርስቶስን መሪያችን ሆኖ በምንጓዝበት ጊዜ፣ በመጨረሻ አጥብቀን ከምንሻው መሸሸጊያ ከመድረስ አንታክትም። ክርስቶስ ራሱ በፊታችን ያለውን አስቸጋሪ መንገድ ረግጦ ለእግራችን መንገዱን አስተካክሎልናል።”“ወደ ዘላለም ሕይወት የሚያደርሰው አቀበታማው መንገድ ሁሉ የደከሙትን በሚያድስ በደስታ ምንጮች የተሞላ ነው።”—Thoughts from the Mount of Blessing, p. 140። 5. ሽልማታችን እና ደስታችን ሐሙስ ፣ መስከረም 14 ሀ. የትኛው የየሱስ ቃል ኪዳን ነው፣ በደስታ እንድንሞላና ለሰማያዊ አባታችን ውዳሴ ለማቅረብ ምክንያት ሊሆነን የሚችለው? ኢሳይያስ 41:10፤ ሉቃስ 12:32፤ 1ኛ ጴጥሮስ 4:13። “እግዚአብሔር ልጆቹ በችግር ብዛት እንዲጎሳቆሉ አይፈቅድም። ጌታችን ፈፅሞ አላታለለንም። እርሱ ለእኛ «መንገዳችሁ ምንም አደጋ ስለሌለ አትፍሩ» አላለንም። እርሱ ፈተናና ችግሮች እንዳሉ ያውቃልና በግልፅ ተናግሯል። እርሱ እኛን ኃጢአትና ጥፋት ካለበት ዓለም ለማውጣት ሳይሆን ዓላማው፣ ወደዘለዓለማዊና ብርቱ መጠጊያችን ወደሆነው ለመምራት ነው።”—Steps to Christ, p. 122፣ 123. ለ. የሱስ የሰጣቸውን ሌሎች አስደናቂ የሰላምና የደስታ ተስፋዎችን ጥቀስ። ዮሐንስ 14:1-3፣ 27፤ 15:11፤ 16:20። “ከፊት ለፊታችን ባለን የሕይወት ዘመን ውስጥ የሚገጥመንን ውጣ ውረድ ከማሰብ ይልቅ ያለፈውንና መጪውንም እያሰብን ‘እስከአሁን ድረስ ጌታ ረድቶናል’ ‘እንደ ዕድሜህ እንዲሁ ኃይልህ ይሆናል’ በማለት እናውጅ (ዘዳ. 33:25)። የሚገጥሙን ፈተናዎች እነርሱን ልንቋቋምበት ከሚሰጠን ጥንካሬ አይበልጡም። ምንም ቢመጣ ከዚያ ተግዳሮት የበለጠ ጥንካሬ እንደሚሰጠን በማመን የተሰጠንን ስራ ባገኘንበት ሁሉ ለመስራት እንትጋ።“የእግዚአብሔር ልጆች «እናንተ የአባቴ ብሩካን ኑ ዓለም ሳይፈጠር በፊት የተዘጋጀላችሁን የእግዚአብሔር መንግስት ውስዱ» (ማቴ. 25:34) የሚሉ በጆሮአቸው የሚያስተጋቡ ፣ ሙዚቃዊ ቃና ያላቸው ፣ ክንጉሱ አፍ የሚፈሱ ክቡር የባርኮት ቃላትን እያደመጡ ሳለ የገነት ደጆች እነርሱን ለመቀበል ወለል ብለው ይከፈታሉ። ማቴዎስ 25:34. . .“ከተዘጋጀልን ዘላለማዊና ባለ ታላቅ ግርማ ውርስ አንጻር ሲታይ «ሰው ስለነፍሱ ምን ዋጋ ሊከፍል ይችላል? ሰው ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን ይሰጣል?› (ማቴ. 16፡26)። . . . ከኃጢአት ተዋጅቶ እና ነፅቶ በሙሉ ኃይሉ ሕይወቱን ለእግዚአብሔር አገልግሎት የሰጠ አንድ ነፍስ (ሰው)በእግዚአብሔር ዓይን ይህ ነው ሊባል የማይችል ክብር (ዋጋ) አለው። እንደዚሁም አንዲት ነፍስ በተዋጃች ጊዜ በላይ በሰማይ በእግዚአብሔር ማደሪያ እና በመላዕክት ዘንድ በቅዱስ የድል ዝማሬ የሚገለጽ ታላቅ ደስታ ይሆናል።”—ibid, p 125፣ 126. የግል ክለሳና የመወያያ ጥያቄዎች አርብ ፣ መስከረም 15 1. መጽሐፍ ቅዱስን የማያውቁትም እንኳን ሳይቀር ሁሉም ሰዎች እውነትን እንዴት ያገኛሉ? 2. ጌታ ለሰዎች ያለውን ያልተገደበ ፍቅር እንዴት ያሳያል? 3. የሱስ መከራውንና ሞቱን ሲጋፈጥ የማረጋገጫ ምንጩ ምን ነበር? 4. ፈተናዎች ሲያጋጥሙን ሰማይ ያዘጋጀልንን ምን ማስታወስ አለብን? 5. በዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ፣ በአማኙ አእምሮ ውስጥ ምን መታወስ አለበት? << >>