ከየሱስ ጋር መራመድ << >> ሰንበት፣ ነሐሴ 16፣ 2018 8ኛ ትምህርት ወደ ክርስቶስ መላት ማደግ የመታሰቢያ ጥቅስ፡- “እግዚአብሔር ለክብሩ የተከላቸው የጽድቅ ዛፎች እንዲባሉ ለጽዮን አልቃሾች አደርግላቸው ዘንድ፥ በአመድ ፋንታ አክሊልን፥ በልቅሶም ፋንታ የደስታን ዘይት፥ በኀዘንም መንፈስ ፋንታ የምስጋናን መጐናጸፊያ እሰጣቸው ዘንድ ልኮኛል።” (ኢሳይያስ 61፡3)። ለንባብ የተመረጠው መጽሐፍ ፡ Steps to Christ, chapter 8፣ pp. 67–75። “ቅርንጫፍ ለማደግ እና ፍሬ ለማፍራት በግንዱ ላይ ጥገኛ እንደሚሆን ሁሉ እናንተም የቅድስና ሕይወት እንድትኖሩ በክርስቶስ ላይ ጥገኞች ናችሁ።”—Steps to Christ, p. 69። 1. የእድገት ቁልፎች እሁድ ፣ ነሐሴ 10 ሀ. ቅዱሳት መጻሕፍት የክርስቲያን እድገትን እንዴት ይገልጻሉ? ኢሳይያስ 61:3፤ 1ኛ ጴጥሮስ 2:2፤ ኤፌሶን 4:14፣ 15፤ ማርቆስ 4:26፣ 27 “የሰው ጥበብ እና ክህሎት ሁሉ ትንሿ የተባለችውን ሕይወት እንኳን ማፍራት አይችልም። እፅዋት ወይም እንስሳት በሕይወት የሚኖሩት እግዚአብሔር ራሱ በሚሰጣቸው ሕይወት ብቻ ነው። ስለዚህ በሰዎች ልብ ውስጥ መንፈሳዊ ሕይወት የሚወለደው ከእግዚአብሔር በሚገኝ ሕይወት ብቻ ነው።”—Steps to Christ, p. 67 ለ. ለእድገት በክርስቶስ ላይ ጥገኛ መሆን እንዳለብን የሚያሳየው ምንድን ነው? ሆሴዕ 14:5–7፤ 1ኛ ቆሮ 3:6፣ 7 “ተወዳዳሪ በሌለው በልጁ ስጦታ፣ እግዚአብሔር አለምን ልክ እንደተከበበችበት አየር በጸጋው ከቧታል። ይህንን ሕይወት ስጪ አየር ለመተንፈስ ፈቃደኞች የሆኑ ሁሉ በክርስቶስ የሱስ ያለውን ሕይወት ይኖራሉ፤ ወደ ሙሉ ሰውነት ደረጃም ያድጋሉ።“ውበትና መልካም አቋም እንዲኖረው አበባ የብርሃን ጨረርን ለማግኘት ወደ ፀሐይ እንደሚያጋድል እኛም የሰማይ ብርሃን በእኛ ላይ እንዲያበራና ባሕርያችን ክርስቶስን ወደ መምሰል እንዲያድግ ወደ ጽድቅ ጸሐይ ፊታችንን ልናዞር ይገባል።”—Ibid., p. 68. 2. የእኛ ረዳት የለሽነት ሰኞ ፣ ነሐሴ 11 ሀ. ጌታችን ምድራዊ አገልግሎቱን ከመጨረሱ በፊት ለደቀ መዛሙርቱ ምን አስፈላጊ ነጥብ ሲናገር አፅንዖት ሰጥቷል? ዮሐንስ 15:4-7 “ብዙዎች በመንፈሳዊ ሕይወት ለማደግ የሚያስፈልገውን ሥራ ቢያንስ የተወሰነውን ክፍል ብቻቸውን የመሥራት ሃሳብ አላቸው። በርግጥ ለኃጢአታቸው ይቅርታን ለማግኘት ክርስቶስን ታምነው የነበረ ቢሆንም፤ መንፈሳዊ ሕይወትን ለመኖር ግን በራሳቸው ጥረት ላይ ይደገፋሉ። ይሁን እንጂ፣ እንዲህ ያለው ጥረት የማይሳካ ነው። የሱስ «ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉም» ብሎናል። የእኛ በፀጋ ማደግ፣ ደስታና ጠቃሚነታችን ሁሉ ከክርስቶስ ጋር በሚኖረን ሕብረት ላይ የተመሰረተ ነው። በፀጋ የምናድገው ከእርሱ ጋር ዕለት ተዕለትና በየሰዓቱ ስንኖር እንዲሁም በእርሱ ውስጥ ስንሆን ነው። እርሱ የእምነታችን ጀማሪ ብቻ ሳይሆን ፈጻሚም ነው። ክርስቶስ ፊተኛውና ኋለኛው እንዲሁም ሁሉ በሁሉ ነው። እርሱ በጅማሬ እና በፍፃሚያችን ላይ ብቻ ሳይሆን በሕይወታችን በእያንዳንዱ እርምጃ ላይ አብሮን ሊሆን ይገባል።”—Steps to Christ, p. 69.“ በክርስቶስ ትምህርት ቤት ራስን ማዋረድንና የልብ ትሕትናን ለመማር ፈቃደኛ ከሆናችሁ፣ በእርግጥም እርሱ እረፍትና ሰላም ይሰጣችኋል። የራሳችሁን ፈቃድና መንገድ መተው እጅግ ከባድ ትግል ነው። ነገር ግን ይህን ትምህርት በመማር፣ እረፍትና ሰላም ታገኛላችሁ። ኩራት፣ ራስ ወዳድነትና ምኞት መሸነፍ አለበት ፤ ፈቃዳችሁ በክርስቶስ ፈቃድ መዋጥ አለበት። መላው ሕይወት አንድ የማያቋርጥ የፍቅር መስዋዕትነት፣ እያንዳንዱ ተግባር፣ እንዲሁም እያንዳንዱ ቃል የፍቅር መግለጫ ሊሆን ይችላል። የወይን ተክሉ ሕይወት በግንድና በቅርንጫፎች በኩል እየተዘዋወረ፣ ታች ወዳሉት ሥሮች ወርዶ ጫፍ እስካሉት ቅጠሎች እንደሚደርስ ሁሉ፣ እንዲሁም የክርስቶስ ጸጋና ፍቅርም ወደ እያንዳንዱ የአካል ክፍሎች መልካምነቱን እየላከ እና እያንዳንዱን የአካልና የአእምሮ ልምምድን (ሥራን) ሁሉ በሙላት እያጥለቀለቀ በነፍስ ውስጥ ይቃጠልና በብዛት ይሰፍናል፣።”—The SDA Bible Commentary [E. G. White Comments], vol. 5, pp. 1091፣ 1092 ለ. በክርስቶስ የማደግ ምስጢሩ ምንድን ነው? ቆላስይስ 2:6፤ ዕብራውያን 10:38። “ሙሉ በሙሉ የእርሱ ለመሆን፣ እርሱን ለማገልገልና ለመታዘዝ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር ሰጥታችኋል፤ ክርስቶስንም እንደ ግል አዳኛችሁ ተቀብላችሁታል። በራሳችሁ ኃጢአታችሁን ልታስተስርዩና ልባችሁንም ልትለውጡ አትችሉም። ነገር ግን ራሳችሁን ለእግዚአብሔር በመስጠት እነዚህን ሁሉ ነገሮች ስለ ክርስቶስ ሲል እርሱ እንዳደረገላችሁ አምናችኋል። በእምነት የክርስቶስ ሆናችኋል። እንደዚሁም በመስጠትና በመቀበል ላይ በተገነባ እምነት በእርሱ ውስጥ ታድጋላችሁ። እርሱን በሁሉም መስፈርቱ ለመታዘዝ ልባችሁን ፈቃዳችሁን፣ አገልግሎታችሁን፤ ራሳችሁንም ባጠቃላይ ሁለንተናችሁን ለእርሱን መስጠት አለባችሁ። ከዚያም ክርስቶስ ጥንካሬያችሁ እንዲሆን፣ ጽድቃችሁና የዘላለም ረድኤታችሁ እንዲሆንላችሁ፣ ለመታዘዝ ኃይል እንዲሰጣችሁ እርሱን ከነሙሉ በረከቱ በልባችሁ እንዲኖር መውሰድ አለባችሁ።”—Steps to Christ, p. 69፣ 70 3. በየዕለቱ መቀደስ ማክሰኞ ፣ ነሐሴ 12 ሀ. የእግዚአብሔር ልጆች በየቀኑ ዕለቱን ሲጀምሩ የሚጠበቅባቸው የመጀመሪያ ግዴታ ምንድን ነው? መዝሙር 5:3። “በማለዳ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር ቀድሱ! ይህ የመጀመሪያ ሥራችሁ እንዲሆን አድርጉ። ፀሎታችሁ «ኦ! ጌታ ሆይ ውሰደኝ፤ ሙሉ በሙሉ የራስህ አድርገኝ! እቅዶቼን ሁሉ በእግርህ ስር አስቀምጣለሁ። ዛሬ ለአገልግሎትህ ተጠቀምብኝ። ከእኔ ጋር ሁንና የማደርገውን ነገር ሁሉ በአንተ እንዳደርገው እርዳኝ›› የሚል ይሁን፡፡ ይህም በየዕለቱ የምንለማመደው ፀሎት ይሁን። በየማለዳው ለዚያን ቀን ራሳችሁን ለእግዚአብሔር ቀድሳችሁ ስጡ። የእርሱ ምሪት በሚያሳያችሁ መሰረት ወይ እንዲከናወኑ አልያም እንዲከሽፉ እቅዶቻችሁን ሁሉ ለእርስ ስጡ። በዚህም መሰረት ዕለት በዕለት ሕይወታችሁን ለእግዚአብሔር እጆች ትሰጣላችሁ፤ ሕይወታችሁም ክርስቶስን ወደ መምሰል እየተለወጠ ይሄዳል።”—Steps to Christ, p. 70. ለ. ክርስቶስ በየቀኑ ምን ግብዣ እያቀረበ ነው? ማቴዎስ 11:28፣ 29። “በክርስቶስ የሆነ ሕይወት የዕረፍት ሕይወት ነው። ምንም አይነት የፍንደቃ ስሜት ላይኖረን ይችላል፣ ነገር ግን በሰላም የተሞላ መታመን ይኖረናል። ተስፋችን በራሳችን ሳይሆን በክርስቶስ ነው። የእኛ ድካም ከእርሱ ብርታት፣ አላዋቂነታችን ከእርሱ ጥበብ፣ ልፍስፍስነታችን ከእርሱ ዘለዓለማዊ ኃይል ጋር ተቆራኝቶአል። ስለዚህም መመልከትና አዕምሮአችን ማተኮር ያለበት በራሳችን ነገር ላይ ሳይሆን፤ ወደ ክርስቶስ ልንመለከት ይገባል። አዕምሮአችን የእርሱን ፍቅር፤ የባሕርይውን ውበትና ፍጽምና ያስብ። ነፍስ ልታሰላስለው የሚገባ ርእስ ቢኖር፤ የክርስቶስ ራሱን መካድ፣ ትህትናው፣ ንጽሕናው፤ ቅድስናው እንደዚሁም ወደር የለሽ ፍቅሩ ሊሆኑ ይገባል። እርሱን በማፍቀር፤ የእርሱ ቅጂ በመሆን ሙሉ በሙሉ በእርሱ ላይ በመደገፍ እርሱን ወደመምሰል ማደግ አለባት። እርሱን ወደ መምሰል የምንለወጠው፣ እርሱን በመውደድ፤ ከእርሱ በመቅዳት፤ እንደዚሁም ሙሉ በሙሉ በእርሱ ላይ በመደገፍ ነው።”—Ibid., pp. 70, 71. ሐ. የአእምሮ ሰላም ለማግኘት ቁልፉ ምንድን ነው? ኢሳይያስ 26:3፣ 4፤ 30:15። “በክርስቶስ ቃል የሚያምኑ፣ ነፍሳቸውንም እርሱ እንዲጠብቅላቸው የሚያስረክቡና ሕይወታቸውን በእርሱ ትእዛዝ መሠረት የሚመሩ ሁሉ ሰላምና ጸጥታ ያገኛሉ። ክርስቶስ አብሮአቸው በመሆኑ ስለሚያስደስታቸው የሚያሳዝናቸው ዓለማዊ ነገር አይኖርም። . . . ሕይወታችን ምስቅልቅል ያለ ይመስል ይሆናል፣ ነገር ግን ራሳችንን ለጠቢቡ ታዋቂ ሠራተኛ (ለየሱስ) ካስረከብን ሕይወታችንንና ባሕርያችንን ለእርሱ ክብር ብቁ እንደሚሆን አድርጐ ያቀነባብረዋል።”“በየሱስ አማካይነት ዕረፍት እንዳገኘን ወዲያውኑ ሰማይ ከዚሁ ይጀምራል። ወደ እኔ ኑና፣ ከእኔ ተማሩ፣ የሚለውን ጥሪ ለመቀበል ስንመጣ የዘላለም ሕይወትን መኖር እንጀምራለን።”—The Desire of Ages, p. 331. 4. ማሰላሰል ለመለውጥ ይረዳል ረቡዕ ፣ ነሐሴ 13 ሀ. አእምሮ ወደ ራስ ከማየት ይልቅ በየሱስ ላይ እንዲያተኩር መፍቀድ ምን ውጤት ያስገኛል? 2ኛ ቆሮንቶስ 3፡18። “ያለ ማቋረጥ በኃይማኖት ዓይን የሱስን በመመልከት ጥንካሬ እናገኛለን። እግዚአብሔር እውነትን ለተራቡትና ለተጠሙት ልጆቹ እጅግ የተከበረውን ምስጢሩን ይገልጽላቸዋል። የሱስ የግል አዳኝ መሆኑን ይረዳሉ። ቃሉን እንደተመገቡ መጠን መንፈስና ሕይወት መሆኑን ይገነዘባሉ። ቃሉ ተፈጥሯዊይውንና ምድራዊይውን ባሕርይ ደምስሶ በየሱስ ክርስቶስ አዲስ ሕይወትን ይሰጣል። ቅዱስ መንፈስም ነፍስን ለማጽናናት ይመጣል። የመለወጥ ኃይል ባለው ጸጋው አማካይነት የእግዚአብሔር ምስል በደቀ መዝሙሩ ላይ ስለሚቀረጽ አማኙ አዲስ ፍጡር ይሆናል። ይህ ሲሆን በጥላቻ ፈንታ ፍቅር ይተካል፣ ልብም የመለኮትን ምሳሌነት ይይዛል።”—The Desire of Ages, p. 391“ አዕምሮ ስለ ራስ ብቻ በሚያስብበት (በሚያተኩርበት) ጊዜ፣ የብርታትና የሕይወት ምንጭ ከሆነው ከክርስቶስ ይርቃል። በመሆኑም የሰይጣን የማያቋርጥ ጥረት፣ ትኩረታችንን ከአዳኛችን ላይ አንስቶ በሌላ ነገር ላይ በማድረግ፣ ነፍሳችን ከክርስቶስ ጋር ያላትን ግንኙነትና አንድነት ማደናቀፍ ነው። ሰይጣን ወደ ዓለም ደስታ፣ የኑሮ ውጣ ውረድ፣ ጭንቀቱና ኃዘኑ እንዲሁም ወደ ሌሎች ሰዎች ስህተት ወይም ወደ እኛ ጥፋትና ፍጹም አለመሆን፣ እነዚህንና እነዚህን ወደ መሳሰሉት ነገሮች ትኩረታችንን ለመቀልበስ ይተጋል። በእርሱ ማታለያዎች መደናቀፍ የለብንም። በእርምጃቸው ጥንቁቆች የሆኑና ለእግዚአብሔር ለመኖር ከልባቸው የሚፈልጉ ብዙ ሰዎች አሉ። ይሁንና ሰይጣን ደግሞ በስህተቶቻቸውና በድክመታቸው ላይ ትኩረታቸውን ዘወትር እንዲያነጣጥሩና ከክርስቶስ እንዲለዩ በማድረግ ድል ሊነሳቸው ተስፋ ያደርጋል። ትኩረታችንን በእኛ በራሳችን ላይ ብቻ በማድረግ «እንድናለን ወይስ አንድንም?» በማለት በጭንቀትና በፍርሀት መዋጥ የለብንም። እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ነፍስን የብርታት ምንጭ ከሆነው ዘወር እንድትል ያደርጋል። ነፍሳችሁን የመጠበቅን አደራ ለእግዚአብሔር በመስጠት በእርሱ ታመኑ። የሱስን አስቡ እርሱን ተጫወቱት፣ በራስ የመመካት ነገር እርሱን በመታመን ይተካ። ጥርጣሬን አስወግዱ፤ ፍርሀትን ሁሉ ደምስሱ፤ በእግዚአብሔር እረፉ።”—Steps to Christ, p. 71፣ 72 ለ. ደቀ መዛሙርቱ ከክርስቶስ ጋር በዕለት ተዕለት የሚስዮናዊነት ሥራ ከሠሩ በኋላ ከመጣው ለውጥ ምን እንማራለን? የሐዋርያት ሥራ 4:13። “[የሱስን] ያለማቋረጥ በመመልከት «... መንፈስ ከሚሆን ጌታ እንደሚደረግ (የእርሱን) መልክ እንመስል ዘንድ ከክብር ወደ ክብር እንለወጣለን› (2ኛቆሮ. 3:18)።“የቀድሞዎቹ ደቀመዛሙርት ውዱን አዳኛቸውን የመሰለብት መንገድ ይህ ነበር። እነዚያ ደቀመዛሙርት የየሱስን ቃል ሲሰሙ ጉድለታቸውን አስተዋሉ። ፈለጉት! አገኙት ከዚያም ተከተሉት። እነዚያ ደቀመዛሙርት ከእርሱ ጋር አንድ ቤት ውስጥ ነበሩ፤ አንድ ላይ በልተዋል። በእልፍኝ ውስጥም በሜዳም ላይ አብረውት ነበሩ። እነርሱም እንደ ተማሪ ሆነው ከመምህራቸው ከየሱስ አንደበት በየዕለቱ የቅዱሱን እውነት ትምህርት ተማሩ። ደቀ መዛሙርቱ «እንደ እኛ የሆነ ሰው» ነበሩ (ያዕ. 5:17)። እነርሱ ልክ እንደእኛ ከኃጢአት ጋር ትግል ውስጥ ነበሩ። ቅዱስ ሕይወት ለመኖር ይችሉ ዘንድ የሚያስፈልጋቸውም ጸጋ ልክ ለእኛ እንደሚያስፈልገው አይነት ነበር።”—ibid, p 72፣ 73 5. ለእኛ የተሰጠን ተስፋ ሐሙስ ፣ ነሐሴ 14 ሀ. የሱስ በጠላት ዓለም ውስጥ ተከታዮቹ ለሚገጥሟቸው ፈተናዎች ምን አስደናቂ ተስፋ ሰጥቷል? ማቴዎስ 28:20። “ክርስቶስ ወደ ላይ ሲያርግ የእርሱ የአብሮነት መንፈስ ግን ከተከታዮቹ ጋር ነበር። ከእነርሱ ጋር የተጓዘው እና የተነጋገረው፤ አብሮአቸው የፀለየው፣ ለልባቸው ተስፋንና መጽናናትን የተናገረው አዳኙ የሱስ የሰላም መልእክት በአንደበቱ ላይ እያለ ነበረ ወደ ላይ የተነጠቀው። ሊቀበሉት በመጡ የመላእክት ደመና ከመሸፈኑ በፊት እንዲህ የሚለው ድምጽ በጆሮአቸው አስተጋባ ፡- «እነሆ እኔ እስከዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ›› (ማቴ. 28:20)።”—Steps to Christ, pp. 73፣ 74. ለ. የሱስ ደቀ መዛሙርቱ በችግር ጊዜ ምን ማድረግ እንዳለባቸው እንዲያውቁ፣ ምን አስፈላጊ መመሪያ ሰጣቸው? ዮሐንስ 16:23፣ 24፤ 14:16-18 “ከእርገቱ በኋላ አንድ ላይ ሲሰበሰቡ፣ በየሱስ ስም ጥያቄያቸውን ለአብ ሊያቀርቡ ጓጉተው ነበር። . . . እንዲህም በማለት የእምነት እጃቸውን ከፍ ከፍ አደረጉ:- «የሞተው፣ ይልቁንም ከሙታን የተነሳው በእግዚአብሔር ቀኝ ያለው፣ ደግሞ ስለእኛ የሚማልደው ክርስቶስ የሱስ ነው» (ሮሜ 8:34)። ጴንጤቆስጤም፣ ክርስቶስ ራሱ «በእናንተ ይኖራል» ያለው እና «እኔ ብሄድ ይሻላችኋል፣ እኔ ባልሄድ አጽናኙ ወደ እናንተ አይመጣምና፤ እኔ ብሄድ ግን እርሱን እልክላችኋለሁ።» ያለውን አጽናኙን ይዞላቸው መጣ። ስለዚህ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ክርስቶስ ያለ ማቋረጥ በመንፈሱ አማካይነት በልጆቹ ውስጥ ይኖራል። ከእርሱም ጋር አሁን ያገኙት ሕብረት፣ እርሱ በአካል ከእነርሱ ጋር ይኖርበት ከነበረው ጊዜ ይልቅ የቀረበ ነበር። በውስጣቸው ያደረው የክርስቶስ ብርሃን፣ ፍቅርና ኃይል በእነርሱ ላይ ይንጸባረቅ ነበርና የተመለከቷቸው ሰዎች «መጽሐፍን የማያውቁና ያልተማሩ ሰዎች እንደሆኑ አስተውለው አደነቁ» (የሐዋ. 4:13)።”—Ibid. pp. 74፣ 75. የግል ክለሳና የመወያያ ጥያቄዎች አርብ ፣ ነሐሴ 15 1. እንደ ተክሎች እያደግን ከሆነ ከሰማይ እርዳታ ለምን ያስፈልገናል? 2. ተክሎች ለማደግ ዝናብ እንደሚያስፈልጋቸው፣ በመንፈስ ለማደግ ምን ያስፈልገናል? 3. እንደ ገልሰብ በየቀኑ መቀደስን አስፈላጊ የሚያደርገው ምንድን ነው? 4. እግዚአብሔር ራስን ከአእምሮአችን አውጥተን ሁልጊዜ በየሱስ ላይ እንድናስብ የሚፈልገው ለምንድን ነው? 5. በእያንዳንዱ አማኝ ሕይወት ውስጥ የዕለት ተዕለት እውን መሆን ያለበት የትኛው ቃል ኪዳን ነው? << >>