እሁድ
ነሐሴ 26
1. ለአስታዋሹ የአዕምሮ አዳራሽ የተሰጠ ተማጽዕኖ
ሀ. ጴጥሮስ ለአስተዋሹ አዕምሯችን ተማጽዕኖውን ያቀረበው እንዴትና ለምን ነበር? 2ኛ ጴጥሮስ 3፡1
“ወንዶችና ሴቶች በሰው ፈንታ በመሞት በሰማይ ግርማ የተከፈለውን የታላቁን መስዋዕት ጥልቀትና ስፋት በሚገባ ማስተዋል ሲችሉ፣ በዚያኔ የማዳን እቅድ እጅግ ከፍ ይላል፣ እናም የቀራንዮ መስቀል ነጸብራቆች በክርስቲያናት ልብ ላይ ለስላሳ፣ የተቀደሰ እና ሕያው ስሜት ማነቃቃት ይችላሉ። ለእግዚአብሔር እና ለበጉ የሚገባው ምስጋናም በልባቸው እና በአንደበታቸው ዘወትር ይሰማል። የቀራንዮን ትዕይንቶች ዘወትር በሚያስታውሱ ልቦች ላይ ኩራት እና በራስ መተማመን ማበብ አይችሉም። ሰውን ለመበዤት የተከፈለውን ታላቁን ዋጋ፣ የእግዚአብሔርን ውድ ልጅ ክቡር ደም ለሚያደንቁ፣ ይህ ዓለም ዋጋ ቢስ ሆኖ ይታያል። አንድን ጠፊ ነፍስ ለመበዤት (ለማዳን) የአለም ሃብት በሙሉ ቢከማች በቂ ዋጋ የለውም። ክርስቶስ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ስለ በደለኛ ሰዎች ኃጢአት ሲሰቃይ ለጠፋው ዓለም የተሰማውን ፍቅር ማን ሊለካው ይችላል? ይህ ፍቅር ሊለካ የማይችል ወሰንም ዲካም የሌለው ነው።”—Testimonies for the Church, vol. 2, p. 212.
“ኦህ፣ በስህተት አቅጣጫ የተመሩ ጉለበቶች ሁሉ፣ በአንድ ታላቅ ዓላማ ላይ ቢውሉ—በዚህ ህይወት ለተበረከቱት ለእግዚአብሔር የጸጋ አቅርቦቶች (ስጦታዎች) ላይ ቢያነጣጥሩ—የእግዚአብሔርን ምሕረት እና ቸርነት እያወራን በማስታወሻ [በአዕምሮ] አዳራሾች ውስጥ ምን አይነት ምስክርነቶችን ባስቀመጥን ነበር! . . ያን ጊዜ፣ ዓለማዊ ግብን ለማሳካት ለምድራዊና ለጊዜያዊ ነገሮች እንደሚሯሯጡ ሰዎች፣ እኛም መንፈሳዊ መዛግብቶችን [ሃብቶችን] ለማከማቸት በንቃትና ኸህ በማይል ትጋት የመጣር ልማዳችን ለዘወትር የሚኖር ህያው መርህ በሆነልን ነበር።”— Our High Calling, p. 188.
ሰኞ
ነሐሴ 27
2. በልቦና (በአስታዋሽ) ማህደራችን ምን እናከማች
ሀ. ለማስታወስ ከሁሉ የሚበልጠው የትኛው ነገር ነው? ለምንስ? 2 ጴጥሮስ 3:2; መዝሙረ ዳዊት 119:11
“አብዛኛውን ጊዜ ፈተናዎች መቋቋም የማይቻሉ ይመስላሉ፤ ምክንያቱም ፀሎትንና የመጽሐፍ ቅዱስን ጥናት ቸል በማለቱ ተፈታኙ ሰው የእግዚአብሔርን ተስፋዎች ወዲያውኑ አስታውሶ በመጽሐፍ ቅዱስ [ጥቅስ] መሳሪያዎች ሰይጣንን መፋለም ስለማይችል ነው። በመለኮታዊ ነገሮች ለመማር ፈቃደኛ በሆኑት በእነርሱ ግን መላእክት በዙሪያቸው ናቸው፤ እጅግ አስፈላጊ በሆነው ሰዓትም፣ አስፈላጊ የሆኑትን፣ ለዚያ ጊዜ ገጣሚ የሆኑትን እውነቶች እንዲያስታውሱ ያደርጋቸዋል። ስለዚህም “ጠላት እንደጽኑ ፈሳሽ ሲመጣ፣ የእግዚአብሔር መንፈስ በእርሱ ላይ ምልክቱን ያነሳበታል” [ኢሳይያስ 59÷19]።
“የሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ተስፋ ሲሰጥ እንዲህ አላቸው፣ “አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል፤ እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል” [ዮሐ 14÷25]። በአደጋ ጊዜ የእግዚአብሔር መንፈስ እንዲያስታውሰን፣ የክርስቶስ ትምህርቶች አስቀድመው በአዕምሮ ውስጥ መከዘን (መጠራቀም) አለባቸው። “አንተን እንዳልበድል” አለ ዳዊት “ቃልህን በልቤ ሰወርሁ” [መዝ 119÷11]። ”—The Great Controversy, pp. 599, 600.
ለ. አእምሯችንን በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክና በአስተምግሮዎቹ ማከማቸት እጅግ በጣም አስፈላጊ መሆኑን የሚያወሱ ምሳሌዎችን ጥቀስ። ሉቃስ 1:67–70; የሐዋርያት ሥራ 3:20, 21
“ሰዎች ካላቸው መጽሐፍት ሁሉ እጅግ ጥንታዊና ከሁሉም በበለጠ ታሪክን አጠቃልሎ የያዘ መጽሐፍ ቢኖር መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው። ከዘላለማዊ የእውነት ፏፏቴ (ምንጭ) ትኩስ ውኃ ሆኖ የሚጎርፍ ሲሆን፣ በዘመናት ሁሉ በንጽህናው ተጠብቆ ይቆይ ዘንድ የመለኮት እጅ ጠብቆ አቆይቶታል። ገና ጥንት በጣም ሩቅ በነበረው፣ የሰው ልጅ የሚደርስበት መስሎት በመመራመር በከንቱ በሚለፋበት እጅግ ጥንታዊ በሆነው ዘመን ሁሉ ላይ ያበራል፡፡ የምድርን መሰረት የመሠረተውን ሰማያትን የዘረጋውን የእግዚአብሔር እጅ መሆኑን ማየት ምንችለው በእግዚአብሔር ቃል ብቻ ነው። ስለ ህዝቦች አመጣጥ እውነተኛ መዛግብት ምንጭ የምናገኘው በዚህ ብቻ ነው፡፡ ስለዘራችን ታሪክ በሰው ትቢት ተንቆ ወይም በቅድመ ውሳኔ የአፃፃፍ ጥላቻ ሳይዛባ መገኘት የሚችለው በዚህ መጽሐፍ ብቻ ነው።”—Education, p. 173.
“አእምሮዬ የብሉይ ኪዳን ታሪክን ስለመጻፍ በታላቅ ሸክም ተሞልቶአል። ወንድሞቼ እና እህቶቼ እጅግ አነስተኛ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ብቻ በዕለቱ ህይወታቸው ማስተሳሰራቸውን ስመለከት በጣም ይጨንቀኛል። ድል አድራጊዎች ለመሆን መዋጋት ያለብን ጦርነት መኖሩን መዘንጋት የለብንም። በሚያበረታው በእግዚአብሔር ጸጋ አማካኝነት ማሸነፍ እንደምንችል እርግጠኞች መሆናችንን ማወቃችን ያስደስተናል (ያስፈነድቀናል)። ከወደቀው ጠላቶች ኃይል ሁሉ ይልቅ እግዚአብሔር እጅግ ይበረታል።”—The Bible Training School, June 1, 1903.
ማክሰኞ
ነሐሴ 28
3. የትንቢት ምልክት ተፈጸመ
ሀ. የብዙዎችን እምነት ለማናጋት በመጨረሻው ዘመን ምን እየሆነ ነው? 2ኛ ጴጥሮስ 3፡3
“ወጣቶችን የማስተማር አጠቃላይ ዘዴ የእውነተኛ ትምህርት መስፈርትን አያሟላም። ያለማመን አስተያየቶች ከትምህርት የመማሪያ መጽሐፍት ርዕሰ-ጉዳዮች ጋር ድርና ማግ ሆነው ተጠላልፈዋል ፤ የእግዚአብሔር ቅዱስ ቃሎችም አጠያያቂ በሆነ አልፎም በተቃውሞ ብርሃን ውስጥ ተቀምጠዋል። ስለዚህ የወጣቶች አእምሮ የሰይጣንን ሐሳቦች ማወቅ ይጀምራል ፤ እናም አንዴ ወደ አዕምሮ የገቡ ጥርጣሬዎች፣ ጥርጣሬውን በተቀበሉት ዘንድ፣ የተረጋገጡ እውነታዎች ይሆናሉ ፤ እንዲሁም ሳይንሳዊ ምርምሮች፣ ግኝቶቹን በሚተረጎሙበት እና ተጣምመው በሚቀርቡበት ሁኔታ ሌሎችን በስህተት ይመራል። ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል በውስን የሰው ችሎት ፊት ለመመዘን ያቀርቡታል ፤ እናም በሰዎች ውስን መለኪያ መሰረት በአምላክ መንፈሳዊ መገለጥ ላይ ፍርድ ይተላለፋል፣ እንዲህም ሲሆን የእግዚአብሔር እውነት በሳይንስ መዝገቦች ፊት እርግጠኛ ያልሆነ ነገር ሆኖ እንዲታይ ተደርጓል። . . . እየተጠራጠሩ በሚገኙት ዘንድ፣ እምነትን ማቀጣጠል ሲችሉ፣ የእግዚአብሔር ቃል ወይም የሳይንስ ግኝት (ውጤት) ተብሎ በውሸት በሚጠራው፣ የትኛው እውነት ስለመሆኑ የራሳቸው ጥርጣሬ ያስገባሉ። መጽሐፍ ቅዱስን ማብራራት እንችላለን የሚሉ ሰዎች ሕያው የሆኑትን ቅዱስ መጽሃፍት ሲያስረዱ፣ በሚያሳዩት ማቅማማት የተነሳ እውነትን በቅን ልቦናቸው የሚያምኑ አማኞች፣ በእምነታቸው እንዲናጉ ተደርገዋል። ሰይጣን የአእምሮን አለማመን (ተጠራጣሪነት) በሚገባ ተጠቅሞበታል ፤ በማይታዩ ወኪሎቹ አማካኝነት አእምሮን በሸንጋይ ፍልስፍናዎቹ ያጨናንቃል ፤ እንዲሁም የሰዎችን አዕምሮ በጥርጣሬ ጭጋግ ይጋርደዋል። ”—Fundamentals of Christian Education, pp. 328, 329.
ለ. በዚህ ረገድ ይህን በተመለከተ ምን የጳውሎስ ምን ምክር ነው ተግባራዊ መሆን የሚችለው? 1 ጢሞቴዎስ 6:20
“የተፈጥሮ አለመሞት (ኢሟችነት) በስፋት የመወያዩበት ርዕስ ሆኖ ቀርባል ፤ እናም አእምሯቸው የጥርጣሬን ድባብ በመረጡ ሰዎች ዘንድ የጥርጣሬ ንድፈ ሐሳቦች በቀላሉ ተቀባይነት አግኝተዋል ፤ ምክንያቱም የሰማይና የምድር መሰረት ከሆነው ከእግዚአብሔር ቅዱስ ሕግ ጋር ስምምነት የሌላቸው ናቸውና፡፡ ወደ ክፋት የሚያዘነብለው ተፈጥሯዊ ዝንባሌያቸው፣ በቀላሉ የውሸት መንገዶችን እንዲመርጡ እና የብሉይም ሆነ የአዲስ ኪዳን መዛግብትንና ታሪክን እውነተኛነት እንዲጠራጠሩ አድርጓቸዋል። ራሳቸው በስህተት ተመርዘው፣ በሌሎች አእምሮ ላይ የጥርጣሬን ዘር ለመዝራት ሊያገኙ የሚችሉትን እያንዳንዱን አጋጣሚ በንቃት ይመለከታሉ። በእነርሱ ዘንድ ተፈጥሮ፣ ከተፈጥሮ አምላክ በላይ ከፍ ያለ ስፍራ ይሰጠዋል፣ ያልተወሳሰበው እምነትም ይጠፋል ፤ ምክንያቱም የእምነት መሠረቱ ያልተረጋገጠ ሆኖ ይታያቸዋልና። በጥርጣሬ ጭጋግ ተጋርዶ፣ የሚጠራጠሩ ሰዎች አእምሮ ከክህደት ዓለቶች ጋር እንዲላተም ችላ ተብሎ ተትቷል። ”—Ibid., pp. 329, 330.
ረቡዕ
ነሀሴ 29
4. የትንቢት መንፈስ የጥቃት ኢላማ ሲሆን [INSPIRATION TARGETED]
ሀ. የቅዱሳን ጽሑፎችን ሥልጣን ከማዳከም በተጨማሪ የሰይጣን ክፉ ጥቃት ትኩረት የሚያደርገው በሌላ በምንድን ነው? ራእይ 12:17; 19፡10።
“ በምስክሮቹ ላይ ያላቸውን የእግዚአብሔርን ሕዝብ እምነት ማዳከም የሰይጣን እቅድ ነው። ከዚያም የእምነታችን እጅግ ወሳኝ ነጥቦች በሆኑት የአቋማችን (የማንነታችን) አዕማዶች ላይ መናፍቅነት ይከተላል ፤ ቀጥሎም በቅዱሳት መጻሕፍት ላይ ጥርጣሬ ይከተልና፣ እየገሰገሱ ቁልቁል መንጎድ ይሆናል። በአንድ ወቅት የታመኑት ምስክሮች በጥርጣሬ አይን መታየት ሲጀምሩ እና ጭራሽ ሲጣሉ፣ የተታለሉ ሰዎች በዚህ እንደማይቆሙ ሰይጣን በደንብ ያውቃል ፤ ወደ ግልጽ ዓመጽ ውስጥ እስኪዘፍቃቸው ድረስ ጥረቱን እጥፍ ድርብ ያደርገዋል፤ ይህም ሊድን በማይችል ውድመት ብቻ የሚደመደም ነው።”—Testimonies for the Church, vol. 4, p. 211. [Author’s emphasis.]
“የመጨረሻው የሰይጣን ማታለል የእግዚአብሔርን መንፈስ ምስክርነት ከንቱ ማድረግ ነው። “ራዕይ ባይኖር ሕዝብ ይጠፋል” (ምሳሌ 29፡18)፡፡ የእግዚአብሔር ቅሬታ ህዝቦች በእውነተኛው ምስክር ላይ ያላቸውን እምነት ለማናጋት በልዩ ልዩ ዘዴዎችና የተለያዩ ወኪሎች እጅግ በረቂቅነት ስራውን ይሰራል። በስህተት ለመምራትና ሐሰተኛውን ከእውነተኛው ጋር ለመቀላቀል፣ እንዲሁም ህዝቦችን በጥላቻ ለመጀቦን፣ የራዕይን ስም የተሸከመው ሁሉ እንደ አክራሪነት እንዲቆጠሩ የውሸት ራዕዮችን አስርጎ ያስገባል ፤ ታማኝ ነፍሳት ግን እውነትንና ሐሰትን በማነጻጸር በሚገባ መለየት እንዲችሉ ያስችላቸዋል። ”—The Faith I Live By, p. 296
ለ. በሦስተኛው መልአክ መልእክት እናምናለን ይሉ የነበሩ ምስክሮቹን መጠራጠር ሲጀምሩ ምን ተፈጠረ— አነርሱስ ይህን ነገር ለምን ብዙ ጊዜ አደረጉ ? ዮሐንስ 3:19, 20
“ያለብህን አደጋ አውቃለሁ። በምሥክሮቹ ላይ የነበረህን እምነት ማጣት ከጀመርህ፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ተንሸራተህ ትወድቃለህ። ብዙዎች የጠያቂነትና የመጠራጠር አቋም እየያዙ መምጣታቸው አስፈርቶኛል፣ እናም ለአንተ ባለኝ ጭንቀት የተነሳ አስጠነቅቅሃለሁ። ስንቶቹ ናቸው ማስጠንቀቂያውን የሚሰሙት? እንደምታውቀውም መስክሮቹን አጥብቀህ ያዝ ፤ ምስክሮቹ በመንገድህ ላይ ጣልቃ ሲገቡ፣ ስህተቶችህን ሲያርሙ፣ ታዲያ በሙሉም ሆነ በከፊል ላለመቀበል ፍፁም ነፃነት ይሰማሃል? በትንሹ ለመቀበል ያ ያቅማማህበት እጅግ በጣም አስፈላጊው ክፍል ነው። እግዚአብሔር እና ሰይጣን በትብብር መቼም ሊሰሩ አይችሉም፡፡ ምስክሮቹ የእግዚአብሔርን ወይም የሰይጣንን ምልክት ይዘዋል። መልካም ዛፍ ክፉ ፍሬ፣ ወይም ክፉ ዛፍ መልካም ፍሬ ማፍራት አይችልም። ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ። እግዚአብሔር ተናግሯል። እናስ በቃሉ ማን ይንቀጠቀጣል ?”— Testimonies for the Church, vol. 5, p. 98.
ሐሙስ
ነሐሴ 30
5. መልእክቶቹን ለዛሬ በመዛግባታችን ማከማቸት
ሀ. እግዚአብሔር በትንቢት መንፈስ አማካኝነት ለህዝቡ የላካቸውን ምስክሮች በተለይም በእነዚህ በመጨረሻዎቹ ቀናት መታዘዝ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው ? ምሳሌ 29:18 (የመጀመሪያው ክፍል) ፤ ሆሴዕ 12:13; 2ኛ ዜና 20፡20 (የመጨረሻው ክፍል)።
“ጌታ ባለፉት ዓመታት የተሰጠው ቀጥተኛው ምስክር እንደገና እንዲታደስ ጠይቋል። ጌታ የመንፈሳዊ ሕይወት ተሐድሶ እንዲካሄድ ጥሪውን ያቀርባል። የህዝቡ መንፈሳዊ ጉልበቶች ለረጅም ጊዜ ሽባ ሆነው ቆይተዋል ፤ ነገር ግን በግልጽ ከሚታየው መንፈሳዊ ሞት ትንሳኤ ሊኖር የግድ ነው። በጸሎት እና ኃጢአትን በመናዘዝ የንጉሱን መንገድ መጥረግና ማዘጋጀት አለብን። ይህን ስናደርግ የመንፈስ ኃይል ወደ እኛ ይመጣል። የጴንጤቆስጤ ሃይል ያስፈልገናል። ይህም ይመጣል ፤ ምክንያቱም ጌታ መንፈሱን ሁሉንም ድል እንደሚነሳ ኃይል አድርጎ ሊልክ ቃል ገብቷልና፡፡
“አስጨናቂ ጊዜያት ከፊታችን ይጠብቁናል። የእውነት እውቀት ያለው ሁሉ ነቅቶ ራሱን፣ ሥጋውን፣ ነፍሱንና መንፈሱን በእግዚአብሔር ተግሣጽ (ስርዓት) ሥር ማድረግ አለበት። ጠላት በዱካችን (በመንገዳችን) ላይ ነው። በሚገባ ልንነቃና ራሳችንን ከእርሱ ልንጠብቅ ይገባናል። የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ መጎናፀፍ ይኖርብናል። በትንቢት መንፈስ የተሰጠውን ምሪት መከተል አለብን። ለዚህ ጊዜ የተሰጠውን እውነትን መውደድ እና መታዘዝ አለብን። ይህም ጠንካራ ማታለያዎችን ከመቀበል ይጠብቀናል፡፡ እግዚአብሔር በቃሉ ተናግሮናል። እርሱ ለቤተክርስቲያን በሰጠው ምስክርነት እና አሁን ያለንበትን ግዴታ እና ልንይዘው የሚገባንን አቋም ግልጽ ለማድረግ በረዱን መጽሃፍቶች አማካኝነት ተናግሮናል። መስመር በመስመር፣ ትእዛዝ በትእዛዝ፣ የተሰጡትን ማስጠንቀቂያዎች በሚገባ ልንታዘዛቸው ያስፈልጋል። ችላ ብንላቸው ምን ሰበብ ልናቀርብ እንችላለን?
“ ለእግዚአብሔር እየለፉ ያሉትን ሐሰተኛውን በእውነተኛው ቦታ እንዳይቀበሉ እለምናለሁ። የሚቀድሰው እውነት መሆን ባለበት ቦታ የሰው ሐሳብ ሊቀመጥ አይገባውም። ክርስቶስ በህዝቡ ልብ ውስጥ እምነትን እና ፍቅርን ለማቀጣጠል በመጠባበቅ ላይ ነው። የተሳሳቱ ንድፈ ሐሳቦች፣ በዘላለማዊ የእውነት መድረክ ላይ ጸንተው መቆም ከሚገባቸው ሰዎች ዘንድ የተቀባይነት ፊት ሊያገኙ አይገባም። በማያጠያይቅ ሥልጣን ላይ የተመሠረቱትን መሠረታዊ መርሆዎች አጥብቀን እንይዝ ዘንድ አምላክ ጥሪውን ያስተጋባልናል። ”—Gospel Workers, pp. 307, 308.
አርብ
መስከረም 6
የግል ግምገማ ጥያቄዎች
1. በተሻሉት ለመተካት በየትኞቹ ትውስታዎች ላይ ነው ማተኮር ያለብኝ?
2. ለማይቀሩት በቀጣዮቹ ለሚገጥሙኝ ፈተናዎች በተሻለ ሁኔታ መዘጋጀት የምችለው እንዴት ነው?
3. የትኞቹ የትምህርቴ ገጽታዎች ናቸው ከእምነቴ ጋር ሊቃረኑ የሚችሉት?
4. የነፍሳት ጠላት ምስክሮቹን ለማጣጣል ቆርጦ የተነሳው ለምንድን ነው ?
5. ለምክሮቹ ጥናት የበለጠ ተገቢ ጊዜ መመደብ እና አድናቆት መስጠት ያለብኝ ለምንድን ነው?