እሁድ
፣ መጋቢት 21
1. ታላቅ ቅንዓት
ሀ. ከእንጀራው ተአምር በኋላ ብዙ ሰዎች ምን ብለው አመኑ? ዮሐንስ 6፡14 ምን ለማድረግስ ጓጉተው ነበር? ዮሐንስ 6፡15 (የመጀመሪያ ክፍል)።
“ይህ እምነታቸው ቀኑን ሙሉ ከሰዓት ወደ ሰዓት እየበረታ መጣ። የሱስ የሠራው ታላቅ ተአምር ለረጅም ዘመን ሲጠበቅ የነበረው ነጻ አውጪ ንጉሥ በመካከላቸው እንዳለ አረጋገጠላቸው። የሰዎቹ ተስፋ ከሰዓት ወደ ሰዓት እየተጠናከረ መጣ። ይሁዳን ማርና ወተት እንደ ውሃ የሚፈስባት ምድራዊ የተድላ ገነት የሚያደርጋት ይህ ሰው ነው አሉ። ማንኛውንም ሰብአዊ ፍላጐት ያሟላል። የተጠሉትን የሮማውያንን ኃይል ያንኮታኩታል። ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን ነጻ ያወጣል። በጦር ሜዳ የሚቆስሉትን ወታደሮች መፈወስ ይችላል። መላውን የጦር ሠራዊትም መመገብ ይችላል። ነገሥታትን ሁሉ አንበርክኮ ለእሥራኤል ሲጠበቅ የኖረውን የግዛት ሥልጣን ሊያስገኝ ይችላል።
“ከመጓጓታቸው ብዛት የተነሳ ሕዝቡ ወዲያውኑ ሊያነግሡት ዝግጁ ነበሩ። ለራሱ ክብር ለማግኘትና የሕዝብን አስተሳሰብ ለመሳብ ምንም ጥረት እንደማያደርግ ተረዱ። ይህን በተመለከተ ከቀሳውስቱና ከመኳንንቱ የተለየ ስለነበረ የዳዊት ዙፋን ይገባኛል ብሎ አይታገልም ይሆናል የሚል ስጋት ነበረባቸው። እርስ በእርሳቸው ከተመካከሩ በኋላ በኃይል የእሥራኤል ንጉሥ አድርገው ሊሰይሙት ተስማሙ። ደቀ መዛሙርቱም መሪያቸው የዳዊት ዙፋን ሕጋዊ ወራሽ ስለመሆኑ ከሕዝቡ ጋር ተስማሙ። ይህን ዓይነት ክብር ከመቀበል እንዲያፈገፍግ የሚያደርገው ትሕትናው ነው ብለው አሰቡ። ስለዚህ ሕዝቡ ራሳቸው ነጻ አውጫቸውን ከፍ ከፍ ማድረግ ነበረባቸው። እነዚያ እብሪተኛ ካህናትና መኳንንት ሳይወዱ በግድ ይህን የእግዚአብሔርን ሥልጣን ተጐናጽፎ የመጣውን ሰው እንዲያከብሩ መሆን አለባቸው።”—The Desire of Ages, pp. 377, 378.
ሰኞ
፣ መጋቢት 22
2. በተሳሳተ መንገድ የሚደረገውን ቅንዓት ማቀዝቀዝ
ሀ. የሱስ ሕዝቡና ደቀ መዛሙርቱ እርሱን በምድራዊ ዙፋን ላይ የማስቀመጥ ዕቅዳቸውን እንዳይፈጽሙ ለመከላከል ምን አደረገ? ዮሐንስ 6፡15
“[ደቀ መዛሙርቱና ሕዝቡ] ዕቅዳቸውን ተግባራዊ ለማድረግ በጉጉት አመቻቹ፣ የሱስ ግን ይካሔድ የነበረውን እንቅስቃሴ በማየት ለእነርሱ ያልተከሰተላቸው የዚያ እንቅስቃሴ ውጤት ምን እንደሚሆን አስተዋለ። በዚያን ወቅት ካህናቱና መኳንንቱ ሕይወቱን ለማጥፋት በማደን ላይ ነበሩ። ሕዝቡን ከእኛ እንዲሸሹ አድርጐአል የሚል ክስ መሠረቱበት። እርሱን በዙፋን ላይ ለማስቀመጥ በሚደረግ ጥረት ሁከትና ብጥብጥ መከተሉ የማይቀር ነበር፤ ይህ ከሆነም የመንፈሳዊዩ መንግሥት ሥራ መተጓጐሉ ነበር። ስለዚህ ያ እንቅስቃሴ ወዲያው መገታት ነበረበት። የሱስ ደቀ መዛሙርቱን ጠራና እርሱ ሕዝቡን ለማሰናበት ወደኋላ እንደሚቀር ጠቅሶ እነርሱ ግን ጀልባቸውን ይዘው ወዲያውኑ ወደ ቅፍርናሆም እንዲመለሱ አዘዛቸው።
“ከዚያ በፊት የሱስ እንደዚህ ለመፈጸም የሚከብድ ትእዛዝ ሰጥቶአቸው አያውቅም። ደቀ መዛሙርቱ የሱስን እንዲነግሥ የሚያደርግ እንደዚህ ያለ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ እንዲነሳ ለብዙ ጊዜ ይመኙ ስለነበር ለዚሁ ተግባርበሕዝቡ መካከል ይታይ የነበረው ጉጉት ከንቱ ይቅር የሚለውን አስተሳሰብ መቀበል አልቻሉም። ለፋሲካ በዓል የተሰበሰቡት ሳዎች አዲሱን ነቢይለማየት ጓጉተው ነበር። የየሱስ ተከታዮች ተወዳጁን ጌታቸውን በእሥራኤል ዙፋን ላይ ለማስቀመጥ አመቺው ወቅት ያንጊዜ መሰላቸው። ምኞታቸው እንደዚያ ተፋፍሞ እያለ የሱስን በምድረ በዳ ላይ ትተው መሔድ ከበዳቸው። ስለዚህ አሳቡን ተቃወሙ፣ የሱስ ግን ከዚያ በፊት በእነርሱ ላይአድርጐት የማያውቀውን በሥልጣን መንፈሱ ተናገራቸው። ከዚያ በኋላ ተቃውሞ ማቅረብ ፋይዳ እንደሌለው በማወቅ ጸጥ ብለው ወደ ባሕሩ ተመለሱ።”—The Desire of Ages, p. 378.
ለ. ተአምሩ በተፈጸመ ማግስት ህዝቡ ምን አደረጉ? ዮሐንስ 6፡22-25
“የእንጀራው ተአምር ወራ በሩቅና በቅርብ ስለተሰራጨ ገና በጥዋት ብዙ ሰዎች የሱስን ለማየት ወደ ቤተሳይዳ ተጓዙ። ቁጥራቸው ብዙ የሆነ ሰዎች በየብስና በባሕር ላይ ተጉዘው መጡ። ከነበረበት ቦታ ወደ ሌላው የባሕርዳርቻ የሚወስደው ጀልባ እንዳልነበረ በማወቅ ባለፈው ምሽት ከተሰናበቱት ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ተአምሩን ከሠራበት ቦታ እናገኘዋለን በማለት ተመልሰው ሔዱ። ከዚያ ሊያገኙት ስላልቻሉ ብዙዎች እርሱን ፍለጋ ወደ ቅፍርናሆም ሔዱ።
ከአንድ ቀን በኋላ የሱስ ጌንሳሬጥ ደረሰ። ከዚያ መድረሱን እንዳወቁ ብዙ ሰዎች «በዚያ አገር ዙሪያ እየተራወጡ ኢየሱስ ወዳለበት ሥፍራ ሁሉ በሽተኞችን በአልጋ ተሸክመው ያመጡ ጀመር።» ማር.6:55።”—Ibid., pp. 383, 384.
ማክሰኞ
፣ መጋቢት 23
3. የተሻለ ዓላማ፣ መለኮታዊ እርዳታ
ሀ. የሱስ ለሕዝቡ ምን ግልጽ ሆኖም ትኩረት የሚስብ መልእክት ነገራቸው? ዮሐንስ 6:26፣ 27
“የሱስ የሰዎቹን የማወቅ ፍላጐት ለማርካት አልሞከረም። እያዘነ «እናንተ” የምትፈልጉኝ እንጀራ ስለበላችሁና ስለጠገባችሁ ነው እንጂ ተአምር ስላያችሁ አይደለም፣» አላቸው። እርሱን የፈለጉት ለተከበረ ዓላማ ሳይሆን እንጀራ እንደተመገቡ ሁሉ ወደ እርሱ በመጠጋት ሌላ ሥጋዊ ጥቅም እናገኛለን በሚል ተስፋ ነው። በተጨማሪም አዳኛችን «ለሚጠፋ ምግብ አትሥሩ፣ ይልቅስ የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ የዘላለም ሕይወት ለሚሆን ምግብ ሥሩ፣» አላቸው። ሥጋዊ ጥቅም ብቻ አትፈልጉ። ዋና ጥረታችሁ መሆን ያለበት ለአሁኑ ሕይወት የሚያስፈልጉ ነገሮችን ለማግኘት ሳይሆን መንፈሳዊ ምግብን ለመመገብና ወደዘላለም ሕይወት የሚቀጥለውን ጥበብ ለመቅሰም ነው።”—The Desire of Ages, p. 384.
ለ. አይሁድ የእግዚአብሔርን ሥራ በተመለከተ የሱስን ምን ጥያቄ ጠየቁት? ዮሐንስ 6፡28 ጌታ የሰጠውን ምላሽ አብራራ። ዮሐንስ 6፡29
“ለጊዜው የሕዝቡ ስሜት ተቀሰቀሰና «ታዲያ የእግዚአብሔርን ሥራ ለመሥራት ምን ማድረግ ይገባናል?» ብለው ጠየቁት። በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን ለማግኘት ሲሉ ብዙ ከባድ ሥራዎችን ሲሠሩ ኖረዋል፣ አሁን ደግሞ የበለጠ ብቁ ሆኖ ለመገኘት አዲስ የአገልግሎት ሥርዓት ካለ ለመስማት ዝግጁ ነበሩ። የጥያቄአቸው መንፈስ ሰማይ ለእኛ ይገባን ዘንድ ምን እናድርግ የሚል ነው። የሚመጣውን ሕይወት ለማግኘት መክፈል ያለብን ዋጋ ስንት ነው?
“የሱስም የእግዚአብሔር ሥራማ እግዚአብሔር በላከው ማመን ነው ሲል መለሰላቸው። የሰማይ ዋጋ የሱስ ነው። ወደ ሰማይ የሚያደርሰው መንገድ «የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ፣» በሆነው ማመን ነው። ዮሐ.1:29።”—Ibid., p. 385.
“ንስሐ ከራስ ወደ ክርስቶስ መመለስ ማለት ነው፤ ክርስቶስን በመቀበል በእምነት እሱ ሕይወቱን በእኛ እንዲኖር መፍቀድ ሲሆን ይህም በመልካም ሥራዎች ይገለጣል።”—Thoughts From the Mount of Blessing, p. 87.
“ጌታ ህዝቡ ሊሰራው የሚገባ ልባዊ ስራ እንዳለ እንዲገነዘቡ ይርዳቸው። . . . በቤት፣ በቤተክርስቲያን እና በአለም ውስጥ የክርስቶስን ስራ መስራት አለባቸው። በርግጥም ብቻቸውን እንዲደክሙ አይተውም። መላእክት ረዳቶቻቸው ናቸው። ክርስቶስም ረዳታቸው ነውና።”— Testimonies for the Church, vol. 8, p. 18.
ረቡዕ
፣ መጋቢት 24
4. የሰማይ እንጀራ
ሀ. አይሁዶች ምን ምልክት ፈለጉ እና የትኛውን ታሪካዊ እውነታ ጠቀሱ? ዮሐንስ 6:30፣ 31 የሱስ ከሰማይ ስለመጣው እንጀራ ምን አለ? ዮሐንስ 6:32፣ 33
“አይሁዶች መናን የሰጠ እርሱ ነው በማለት ድርጊቱን የፈጸመውን ጌታ ረስተው መሣሪያ የሆነውን ሙሴን ያከብሩት ነበር። አባቶቻቸው በሙሴ ላይ አጉረመረሙ፣ መለኮታዊ ተልዕኮውንም ተጠራጠሩ፣ ካዱትም። አሁንም ልጆቻቸው በዚያው መንፈስ የእግዚአብሔርን መልእክት ያመጣላቸውን ጌታ ናቁት። «በዚህ ጊዜ የሱስ እንዲህ አላቸው። ከሰማይ የወረደውን እንጀራ የሰጣችሁ ሙሴ አይደለም።» መናውን የሰጣቸው ከመካከላቸው ቆሞ ነበር። ዕብራውያንን በምድረ በዳ የመራቸውና በየቀኑ ከሰማይ በወረደ ምግብ የመገባቸው ራሱ ክርስቶስ ነበር። ያ ምግብ የእውነተኛው ሰማያዊ ምግብ ምሳሌ ነበር። እውነተኛው መና ወሰን ከሌለው ከእግዚአብሔር ፍጹምነት የሚፈልቀው ሕይወት ሰጪ መንፈስ ነው።”—The Desire of Ages, pp. 385, 386.
ለ. አእምሯቸው በተፈጥሯዊ፣ በሚታየው እንጀራ ላይ ብቻ በማተኮር ምን ልመና አቀረቡ—ጌታስ ምን ገለጸላቸው? ዮሐንስ 6፡34-36
“የሱስ የተጠቀመበት የንግግር ዘይቤ በአይሁዶች ዘንድ የተለመደ ነበር። ሙሴ በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ «ሰው ሕይወቱ ተጠብቆ መኖር የሚችለው እግዚአብሔር በሚናገረው ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አለመሆኑን ሊያስተምርህ ነው፣» ብሎአል። ነቢዩ ኤርምያስም «ቃልህ ወደ እኔ እኔ በመጣ ጊዜ በላሁት፣ ልቤንም በደስታና በሐሴት ሞላው፣» ሲል ጽፎአል። ዘዳ.8:3፤ ኤር.15:16። ራሳቸው የአይሁድ ምሑራን እንጀራ መመገብ መንፈሳዊ ትርጉሙ ሕግን ማጥናትና ጥሩ ሥራ መለማመድ” እንደሆነና መሲሑ ሲመጣ ሕዝበ እሥራኤል በሙሉ እንደሚመገቡ ይናገሩ ነበር። የነቢያት ትምህርት ከእንጀራው ተአምር የሚገኘውን ጥልቅ የሆነ መንፈሳዊ ትምህርት ግልጽ አድርጐ አስቀምጦታል። የሱስ በምኩራቡ ሲያዳምጡት ለነበሩት ሰዎች ግልጽ ለማድረግ የፈለገው ይህን ትምህርት ነበር። ቅዱሳት መጻሕፍትን በትክክል ተረድተው ቢሆን ኖሮ የሱስ «የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ፣» ያለውን ማስተዋል ይችሉ ነበር። ያ ሁሉ ሕዝብ የሱስ የሰጣቸውን ምግብ የበሉት ባለፈው ቀን ነበር። ከዚያ ምግብ ሥጋዊ ብርታትና ተሐድሶ እንዳገኙት ሁሉ እንደዚሁም ከክርስቶስ ለዘላለም ሕይወት የሚሆን መንፈሳዊ ብርታት ማግኘት ይችሉ ነበር።”—Ibid., p. 386.
ሐሙስ
፣ መጋቢት 25
5. ትንሳኤ እና የዘላለም ህይወት
ሀ. ራሳቸውን ከክርስቶስ ጋር አንድ ለሚያደርጉ ምን ሁለት ተዛማጅ ተስፋዎች ተሰጥተዋል—ይህስ ለእያንዳንዱ ኃጢአተኛ ተስፋ የሚያመጣው እንዴት ነው? ዮሐንስ 6፡37-40
“[የሱስ] እርሱን በእምነት የተቀበሉት ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖራቸው እንጂ አንድም እንኳ እንዳይጠፋ ቃል ገብቷል።”—The Desire of Ages, p. 387.
“ወደ እግዚአብሔር ለመምጣት ብቁ እስክትሆን ድረስ ራስህን እስክትሻሽል ድረስ ከክርስቶስ እንድትርቅ የሚናገረውን የጠላትን ምክር አትስማ። እንደዚያ እስክትሆን ድረስ ከጠበቅህ፣ በጭራሽ አትመጣም፡፡ ሰይጣን ወደ ቆሻሻ ልብስህ ሲጠቁም፣ ‘ወደ እኔ የሚመጣውን ከቶ ወደ ውጭ አላወጣውም’ የሚለውን የየሱስን ተስፋ ደግመህ (ዮሐንስ 6፡37) አስታውስ። የየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ እንደሚያነጻ ለጠላት ንገረው። “እጠበኝ፥ ከበረዶም ይልቅ ነጭ እሆናለሁ”፤ የሚለውን የዳዊትን ጸሎት የራስህ አድርግ። መዝሙረ ዳዊት 51:7
“ተነሥተህ ወደ አባትህ ሂድ። ገና በጣም ሩቅ ሳለህ እሱ ወጥቶ ይቀበልሃል። በንስሐ ወደ እርሱ አንድ እርምጃ እንኳን ከቀረብክ፣ እርሱ ወሰን በሌለው ፍቅር እቅፍ ውስጥ ሊያስገባህ ይቸኩላል። ለተጸጸተች ነፍስ ጩኸት ጆሮው ክፍት ነው። እግዚአብሔር የመፈለግ የልብ መነካት ገና ጅማሮ ላይ እንኳ በእርሱ ዘንድ የታወቀ ነውና። ማንኛውም ከምንቀጠቀጥ ከንፈር እንኳን ቢሆንም የወጣ ጸሎት፣ ማንኛውም በሚስጥር የፈሰሰ እንባ፣ ማንኛውም በፍጹም ቅን ልብ እግዚአብሔርን የመፈለግ ጥያቄ፣ ምንም ያህል ደካማ ቢሆኑም፣ የእግዚአብሔር መንፈስ ግን እነዚህን ጥያቄዎች ለመቀበል ሊገናኘው ይወጣል። ጸሎቱ ከመቅረቡ ወይም የልብ መሻት ከመገለጹ በፊትም እንኳ የክርስቶስ ጸጋ በሰው ነፍስ ላይ የሚሠራውን ጸጋ ለማግኘት ይወጣል።”—Christ’s Object Lessons, pp. 205, 206.
ለ. የማያምኑት አይሁዶች ምን አጉረመረሙ እና የሱስ በእርሱ ለሚያምኑት ምን ተስፋ ደግሞ ሰጣቸው? ዮሐንስ 6፡41–51
አርብ
፣ መጋቢት 26
የግል ግምገማ ጥያቄዎች
1. ከእንጀራው ተአምር በኋላ የክርስቶስ ተከታዮች ምን ለማድረግ አስበው ነበር?
2. የሱስን እየተከተሉ ያሉት የብዙዎች ፍላጎት ምን እንደሆነ ግለጽ።
3. በዮሐንስ 6፡29 ያለውን የየሱስን ቃል አብራራ።
4. ክርስቶስ የመንፈሳዊ ሕይወትን ምንጭ ለማመልከት የተጠቀመው ምሳሌ ምንድን ነው?
5. የአይሁድ መሪዎች ለክርስቶስ ያላቸውን ጭፍን ጥላቻ ያሳዩት እንዴት ነው?