Back to top

Sabbath Bible Lessons

ወንጌል እንደ ዮሐንስ መሠረት (ፍል ሁለት)

 <<    >> 
4ኛ ትምህርት ሰንበት፣ ሚያዚያ 18፣ 2017

እንደዚህ ሰው ማንም ከቶ አልተናገረም

የመታሰቢያ ጥቅስ፡- “ሎሌዎቹ። እንደዚህ ሰው ማንም እንዲሁ ከቶ አልተናገረም ብለው መለሱ።” (ዮሐ. 7፡46)።

“የሱስ እውነትን ለመቀበልና በትክክል ለማስተዋል ከሕሊናዊ አስተሳሰብ ይልቅ የሚያስፈልገው የልብ ዝግጁነት መሆኑን ተናገረ። እውነት በነፍስ ተቀባይነትን ማግኘትና በልብም መከበርን ይጠይቃል።”—The Desire of Ages, p. 455.

ለንባብ የተመረጠዉ መጽሐፍ፡   Testimonies to Ministers, pp. 506–512. 

እሁድ ፣ ሚያዚያ 12

1. የሰዎች ፍላጎት በየሱስ ላይ

ሀ. አንዳንድ አይሁዳውያን የሱስን በግልጽ ሲሰብክ ሲሰሙና ሲያዩ ምን ብለው ጠየቁ? ዮሐንስ 7:25፣ 26

“የየሱስን ንግግር ያዳምጡ ከነበሩት ሰዎች መካከል ብዙዎቹ በኢየሩሳሌም የሚኖሩና የባለሥልጣኖቹንም ሴራ የሚያውቁ ሲሆኑ ምንም ነገር ሊገታው በማይችል ኃይል ወደ የሱስ ተሳቡ። የሱስ የእግዚአብሔርልጅ ስለመሆኑ እምነታቸው ጽኑ ነበር።”—The Desire of Ages, p. 457.

ለ. ሰይጣን በገዢዎቹ ላይ ጥርጣሬ እንዲፈጠር የሠራው እንዴት ነው? ዮሐንስ ወንጌል 7፡27

“ሰይጣን ጥርጣሬ እንዲያድርባቸው ለማድረግ ዝግጁ ነበር፣ ለዚህም ሰዎቹ ስለ መሲሑና ስለ አመጣጡ የነበራቸው የተሳሳተ ግንዛቤ አመቺ ሁኔታ ፈጠረለት። በዚያን ጊዜ ክርስቶስ በቤተልሔም እንደሚወለድ፣ ከጥቂት ጊዜ በኋላ እንደሚሰወርና ሁለተኛ ሲገለጥ ከየት እንደመጣ ማንም አያውቅም ተብሎ ይታመን ነበር። መሲሑ የሰብአዊነት ባሕርይ አይኖረውም ብለው የሚያምኑም ጥቂት አልነበሩም። የናዝሬቱ የሱስ በሕዝቡ አስተሳሰብ መሠረት መሲሑ ይኖረዋል ተብሎ የተጠበቀው ክብር ስላልታየበት ብዙ ሰዎች «ታዲያ እኛ ይህ ሰው ከወዴት እንደሆነ እናውቃለን፣ መሲሕ ሲመጣ ግን ከወዴት እንደሆነ የሚያውቅ ማንም የለም፣» አሉ።—Ibid.


ሰኞ ፣ ሚያዚያ 13

2. ተንኮል አዘል እቅዶች ተቀለበሱ

ሀ. የሱስ የተጠራጠሩትን አድማጮቹን ሐሳብ ባነበበ ጊዜ ምን አላቸው? ዮሐንስ 7፡28

“ሰዎቹ እንደዚህ በጥርጣሬና በእምነት መካከል በሚዋልሉበት ጊዜ የሱስ ከአስተሳሰባቸው በመነሳት «እኔን ታውቁኛላችሁ፣ ከወዴትም እንደመጣሁ ታውቃላችሁ፣ ነገር ግን እኔ በራሴ ሥልጣን አልመጣሁም፣ የላከኝ እውነተኛ ነው፣ እናንተም አታውቁትም፣» በማለት መለሰላቸው። የክርስ ቶስን መነሻ የሚያውቁ ይመስላቸው ነበር። ነገር ግን እርሱ ከየት እንደመጣ ፈጽሞ የሚያውቁት ነገር አልነበረም። እነዚህ ሰዎች እግዚአብሔርየሚፈልገው ዓይነት ሕይወት ኖረው ቢሆን ኖሮ ልጁ በተገለጠላቸው ጊዜ ሊያውቁት ይችሉ ነበር።”—The Desire of Ages, p. 457.

ለ. የሱስን ለመቃወም የሚያስችል መከራከሪያ ስለሌለ፣ የአይሁድ መሪዎች እሱን ዝም ለማሰኘት የሞከሩት በምን መንገድ ነው? ዮሐንስ 7፡30 (የመጀመሪያ ክፍል)። ታዲያ፣ ለምን ሊይዙት አልቻሉም? ዮሐንስ 7፡30 (የመጨረሻው ክፍል)።

“አዳማጮቹ ክርስቶስ የተናገራቸውን ቃላት በሚገባ አስተውለዋል። ይህ ንግግር የሱስ ከብዙ ወራት በፊት በአይሁድ ብሔራዊ ሸንጐ ፊት እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ ስለመሆኑ የተናገረው ንግግር ማጠናከሪያ ነበር። በዚያን ጊዜ ባለሥልጣኖቹ የየሱስን ሕይወት ለማጥፋት ባቀዱት መሠረት አሁን ሊይዙት ፈልገው ነበር። ነገር ግን አንድ የማይታይ ኃይል ከዚህ ማለፍ አትችሉም በማለት አገዳቸው።”—Ibid.

ሐ. ብዙዎች በየሱስ ላይ ያላቸውን እምነት የገለጹት እንዴት ነው—ገዥዎቹስ በሕዝቡ ዘንድ ለእርሱ ያለውን ቦታ ሲገነዘቡ ምን ለማድረግ አሰቡ? ዮሐንስ 7:31፣ 32

“ሁኔታውን በጉጉት ይከታተሉ የነበሩት የፈሪካውያን መሪዎች ሕዝቡ ለየሱስ ያሳይየነበረውን የድጋፍ መግለጫ ተመለከቱ። በፍጥነት ወደ ካህናት አለቆቹ ሒደው እርሱን የሚይዙበትን ዕቅድ አመቻቹ። ከሕዝቡ መካከል ሊይዙት ስላልደፈሩ ብቻውን በሚሆንበት ጊዜ ሊይዙት ተዘጋጁ።”—Ibid., pp. 457, 458.


ማክሰኞ ፣ ሚያዚያ 14

3. ግብዣው

ሀ. በበዓሉ የመጨረሻ ቀን የሱስ በኃጢአት የደከሙትን ነፍሳት ለማጽናናት የተጠቀመው ግሩም ምሳሌ ምንድን ነው? ዮሐንስ 7:37፣ 38

“የእግዚአብሔርን ቃል የሚቀበል ልብ በጸሐይ እንደሚደርቅ እቋሪ ውሃ ወይም እንደሚያፈስ ባሊ አይደለም። የተጠሙትን ሁሉ እንደሚያረካ፣ የደከሙትን እንደሚያበረታ ከተራራ ስር መንጭቶ በቋጥኞች መካከል እየተጣራ ሳያቋርጥ እንደሚወርድ ወንዝ ነው። አወራረዱ ጥልቅ ሆኖ ውኃው መሬትን ሁሉ እንደሚያጠጣ ወንዝ ነው። እያዜመ የሚወርደው ውኃ በመንገዱ ፍሬን እያበረከተ ያልፋል። በዳሩ የሚገኘው ስር የለመለመ ዛፎች ቅርንጫፋቸው የበዛ፣ አበባዎቹም በጣም የፈኩ (የደመቁ) ይሆናሉ። መሬት በድርቅ ምክንያት አቧራ ስትሆን የወንዙ ዳር ግን ለምለም ይሆናል።

“እውነተኛ የእግዚአብሔር ልጅም እንዲሁ ነው። የክርስቶስ ሃይማኖት ሕይወትን ያድሳል።ሕያውና መንፈሳዊ ጉልበት ነው። ልብ የሰማያዊውን ዕውነታዊ ተፅዕኖ ሲቀበልና በፍቅር ሲሞላ እንደነዚህ ውኖች በምድረ በዳ መካከል እየወረደ በድርቅ ፋንታ ልምላሜንና ፍሬን የሚያስገኝ የውኃ ቦይ (መስኖ) ይመስላል።”—Prophets and Kings, pp. 233, 234

“ ‘ማንም ሰው የሚያረጋጋ ተስፋን፣ ከኃጢአት ዝንባሌ መዳንን ቢጠማ፣ ክርስቶስ ‘ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ’ ይላል። ዮሃንስ 7:37።”—The Ministry of Healing, p. 179.

ለ. ይህን ግብዣ የበለጠ ለመረዳት የሚቻለው እንዴት ነው? ዮሐንስ 7፡39

“ክርስቶስ የእውነትን መርሆች በወንጌል አቅርቧል። በእርሱ ትምህርት ከእግዚአብሔር ዙፋን የሚፈሱትን ንጹህ ጅረቶች እንጠጣለን።”—Testimonies for the Church, vol. 8, p. 309.

“እኛ የምንፈልገው ሕያው ሃይማኖት ነው። ነፍሱ ከእግዚአብሔር ጋር የተቆራኘችለት እና ለክርስቶስ በቅንዓት የተሞላ ስለ ግዴታው ሰፊ መረዳት ያለው አንድ ተራ ሰው ለበጎ ነገር የሚሆን በጎ ተጽዕኖ ያሳድራል። ከንጹሕ፣ ከምንጩ አጠገብ ካለው ውሃ እንጂ የተበላሸ፣ የደፈረሰና የረከሰውን ወንዝ አይጠጣምና አዲስ መንፈስ እና ኃይልን ለቤተ ክርስቲያን ማስተላለፍ ይችላል፡፡ ከውጪ የሚመጣው ጫና እየጨመረ ሲሄድ፣ እግዚአብሔር በሚያምኗቸው በተቀደሰ፣ ጥብቅ እውነቶች ቤተ ክርስቲያኑን ያበረታታል። ከሰማይ የወረደው መንፈስ ቅዱስ ከእግዚአብሔር ወንዶችና ሴቶች ልጆች ጋር በመሥራት እንቅፋቶችን በማለፍ በጠላት እጅ ውስጥ ያለውን ምሽግ ይይዛል። አምላክ እውነትን ለሚወዱና ትእዛዛትን ለሚጠብቁ ሰዎች ታላቅ ድሎችን ይሰጣል።”—Ibid., vol. 5, p. 581.


ረቡዕ ፣ ሚያዚያ 15

4. እንደሌሎቹ ያልሆኑ ቃላት

ሀ. ክርስቶስ ስለሕይወት ውኃ ያለውን በመጥቀስ ብዙዎች ምን መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል—ለምንስ? ዮሐንስ 7፡40 (ከዘዳግም 18፡15 ጋር አወዳድር)።

ለ. አንዳንዶች እንዲህ ባለው ተስፋ ተነሳስተው ሳለ ሌሎችስ ምን ምላሽ ሰጡ? ዮሐንስ 7፡41-44

ሐ. መኮንኖቹ ከአለቆቻቸው ምን ትዕዛዝ ተቀበሉ? ዮሐንስ 7፡45 ራሳቸው የሱስን መያዝና ማምጣት ያልቻሉት ለምንድን ነው? ዮሐንስ 7፡46

“የሱስን ለመያዝ በካህናቱና በሹማምንቱ ተልከው የነበሩት ሰዎች በበዓሉ መጨረሻ ቀን ባዶ እጃቸውን በተመለሱ ጊዜ «ስለምን አላመጣችሁትም?» የሚል የቁጣ ጥያቄ ቀረበላቸው። እነርሱም ኮስተር ብለው «ይህ ሰው እንደሚናገረው ዐይነት ማንም ተናግሮ አያውቅም፣» ብለው መለሱላቸው።

“ደንዳናው ልባቸው በየሱስ ቃል ተነካ። እርሱ በቤተ መቅደሱ አደባባይንግግር በሚያደርግበት ጊዜ እርሱን ለመክሰስ የሚያስችል ነገር በመሻት በአካባቢው ሲያንዣብቡ ቆዩ። ንግግሩን በተመስጦ በማዳመጥ የተላኩበትን ተግባር ረሱት። ክርስቶስ ለነፍሳቸው ተገለጠላቸው። ካህናቱና ? ባለሥልጣናቱ ሊያዩት ያልቻሉት ሰብአዊነት በመለኮት ክብር ተጐናጽፎ አዩ።”—The Desire of Ages, p. 459.

“[ክርስቶስ] መለኮታዊውን እውነት ለማስረዳት የሚያውቁትን የተፈጥሮ ነገር ተጠቅሟል። በዚህ መንገድ ጥሩውን ዘር ለመቀበል የልብ አፈር ተዘጋጅቷል፡፡ አድማጮቹ የእሱ ፍላጎቶች ከነሱ ጋር አንድ እንደሆኑ፣ በደስታቸው እና በሀዘናቸው ልቡ አብሯቸው እንደሚመታ እንዲሰማቸው አድርጓል። በተመሳሳይ ጊዜ እጅግ ከተከበሩ መሪዎቻቸው መካከል ከሁሉም የሚበልጠዉ እንኳን ካለው ይልቅ እጅግ የላቀ የኃይል እና ክብር በእርሱ እንዳለም ተመልክተዋል። የክርስቶስ አስተምህሮዎች ከዚህ በፊት በማያውቋቸው ቀላልነት፣ ክብር እና ሃይል ያላቸው ነበሩ፣ እናም ያለፈቃዳቸው ከአፋቸው የሚወጣው ጩኸታቸው፡- ‘እንደዚህ ሰው ማንም እንዲሁ ከቶ አልተናገረም’ የሚል ነበር። ሕዝቡ በደስታ ያዳምጡት ነበር፤ ነገር ግን ራሳቸውን የእውነት ጠባቂዎች አድርገው በውሸት የሚያምኑት ካህናቱና አለቆቹ ህዝቡን ከእነርሱ ለይቶ የሕይወትን ብርሃን እንዲከተሉ ባደረገው በእርሱ ስለ ተገለጠው ጸጋ ክርስቶስን እርሱን አምርረው ጠሉት። የአይሁድ ነገዶች በእነሱ ተጽዕኖ ምክንያት መለኮታዊውን ባሕርይ ማወቅ ባለመቻላቸው አዳኙን አልተቀበሉም።”—Testimonies for the Church, vol. 5, p. 747.


ሐሙስ ፣ ሚያዚያ 16

5. በቅንነት የሚፈልግ እየበረታ ሄደ

ሀ. የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን ሎሌዎቹን እንዴት ገሠጹአቸው? ዮሐንስ 7፡47-49

ለ. ከኒቆዲሞስ ጋር የተካሄደውን ውይይት አብራሩ—በዮሐንስ ምዕራፍ 3 ከክርስቶስ ጋር በምሽት ንግግር ካደረገበት ጊዜ ጀምሮ ያለውን እድገት ያሳያል። ዮሐንስ 7፡50–52።

“[ኒቆዲሞስ] እውነትን በልቡ ደበቀ፣ እናም ለሦስት ዓመታት ያህል ብዙም በግልጽ የማይታይ ፍሬ ነበረው። ይሁን እንጂ ኒቆዲሞስ ለክርስቶስ በይፋ እውቅና ባይሰጥም በአይሁድ መማክርት ሸንጎ ውስጥ ካህናት እሱን ለማጥፋት ያደርጉት የነበረውን ዕቅድ ደጋግሞ አከሽፏል።”— The Acts of the Apostles, p. 104.

“ክርስቶስ ለኒቆዲሞስ [በዮሐንስ ምዕራፍ 3 ላይ በምሽት ጉብኝት ወቅት] የሰጠው ትምህርት ከንቱ አልነበረም። ፅኑ እምነት በልቡ ላይ ተጣብቆ ነበር፣ እና በልቡ የሱስን ተቀብሏል። ከአዳኝ ጋር ካደረገው ቃለ ምልልስ ጀምሮ ፣ የብሉይ ኪዳንን ቅዱሳት መጻሕፍት በትጋት መርምሯል፣ እናም እውነት በወንጌል እውነተኛ መቼት (ጊዜና ቦታ) ውስጥ በትክክል ሲቀመጥ አይቷል።

“በእሱ የጠየቀው ጥያቄ ጥበብ የተሞላበት ነበር፣ እናም በጠላት ባይተታለሉ ኖሮ በሸንጎው ውስጥ የነበሩትን ሁሉን የሚያሳምንም ነበር። ነገር ግን በጭፍን ጥላቻ ተሞልተው ስለነበር የናዝሬቱን የሱስን የሚደግፍ ምንም ዓይነት ክርክር ምንም አሳማኝ ቢሆን በእነርሱ ዘንድ ተቀባይነትት አልነበረውም። ኒቆዲሞስ ከነሱ ያገኘው መልስ፡- “አንተም ደግሞ ከገሊላ ነህን? ነቢይ ከገሊላ አይነሣምና መርምርና እይ” የሚል ነበር።

“ካህናቱና አለቆቹ ክርስቶስ ከገሊላ እንደ ወጣ እንዲያምኑ ሰይጣን ባቀደው እቅድ እነሱም መሠረት እነሱም ተታለሉ። በቤተልሔም እንደተወለደ የሚያውቁ አንዳንዶች ግን እነሱ ከተናገሩ ይህ የውሸት ክስ ኃይሉን እንዳያጣ በመስጋት ዝም አሉ።”—The SDA Bible Commentary [E. G. White Comments], vol. 5, p. 1136.


አርብ ፣ ሚያዚያ 17

የግል ግምገማ ጥያቄዎች

1. የሱስ የሰዎችን ትኩረት የሳበው ለምንድን ነው?

2. የአይሁድ ገዥዎች የሱስን ለማስቆም ያደረጉትን ጥረት የቀጠሉት እንዴት ነው?

3. የሱስ በበዓሉ የመጨረሻ ቀን ምን ግልጽ ጥሪ አቅርቧል?

4. በዚህ ምክንያት የተፈጠረውን ታላቅ ውዝግብ አስረዳ።

5. የማውቃቸውን ሰዎች ሳስብ፣ ስለ ኒቆዲሞስ ምን ማስታወስ አለብኝ?

 <<    >>