እሁድ
፣ ግንቦት 24
1. ዳግም የምርመራ ጥያቄ
ሀ. የሱስ አይኑን ያበራለትን ወጣት ለሁለተኛ ጊዜ አስጠርተው ፈሪሳውያን ምን እንዲያደርግ ሊያስገድዱት ሞከሩ? ዮሐንስ 9፡24
“ፈሪሳውያን የሱስ የፈጸመውን ድርጊት በሕዝቡ ዘንድ ታዋቂነት እንዲያገኝ ማድረጋቸውን ተገነዘቡ። ተአምሩን መካድ አልቻሉም። ዓይነስውር የነበረው ሰው በደስታና በአመስጋኝነት መንፈስ ተሞላ፣ አስደ ናቂውን ሥነ ፍጥረት ተመለከተ፣ በሰማይና በምድር ውበትም ተደሰተ። ስለተደረገለት ነገር ያለ ስጋት ተናገረ፣ ፈሪሳውያኑ ግን «አንተ እውነቱን በመናገር እግዚአብሔርን አክብር፣ ይህ ሰው ኃጢአተኛ መሆኑን እኛ እናውቃለን» በማለት ዝም ሊያሰኙት ሞከሩ። ይህን ማለታቸው እግዚአብሔር እንጂ ይህ ሰው የዓይኔን ብርሃን ሰጠኝ አትበል ለማለት ነው።”—The Desire of Ages, p. 473.
ለ. ወጣቱ ምን የማያዳግም መከራከሪያ አቀረበ? ዮሐንስ 9፡25
ሰኞ
፣ ግንቦት 25
2. ዳግም የምርመራ ጥያቄ (የቀጠለ)
ሀ. ፈሪሳውያን ዓይኑ የበራለትን ወጣት እንደገና ምን ብለው ጠየቁት? ዓላማቸውስ ምን ነበር? ዮሐንስ 9፡26
“[ፈሪሳውያን]ያን ጊዜ እነርሱ «ምን አደረገልህ? ዓይኖችህንስ ያዳነው እንዴት ነው?» አሉና ጠየቁት። ተሞኝቻለሁ ብሎ እንዲያምን ለማድረግ በቃላት ጋጋታ ግራ ሊያጋቡት ሞከሩ። ሰይጣንና መላእክቱ በፈሪሳውያኑ ጐን በመሆን የየሱስን ታዋቂነት ለመቃረን ኃይላቸውንና ስውር ደባቸውን ከሰው እስተሳሰብ ጋር አጣምረው ተሰለፉ። በብዙ ሰዎች አእምሮ የነበረውን የእምነት ስሜት አደነዙት።”—The Desire of Ages, p. 473.
ለ. ወጣቱ እንዴት መለሰላቸው—እና እሱን ለማበረታታት ከጎኑ ማን ቆመው ነበር? ዮሐንስ 9፡27
“የዓይኑ ብርሃን የተመለሰለትን ሰው ለማበረታታት የእግዚአብሔር መላእክት ከዚያው ቦታ ነበሩ።
“ፈሪሳውያኑ እውር ሆኖ ከተወለደው መሐይም ሰው ሌላ የተጋፈጣቸው ኃይል መኖሩን አልተገነዘቡም፤ ከማን ጋር ክርክር እንደገጠሙም አላወቁም። መለኮታዊ ብርሃን ዓይነስውር ወደ ነበረው ሰው ነፍስ ሰርጾ ገባ። እነዚያ ግብዞች እምነቱን ሊያስጥሉት በሚሞክሩበት ጊዜ ኃይለኛና ቀጥተኛ መልስ በመስጠት በወጥመዳቸው እንደማይያዝላቸው ለማሳየት እንዲችል እግዚአብሔር ረዳው።”—Ibid., pp. 473, 474.
ሐ. በዛሬው ጊዜ ተመሳሳይ እርዳታ እንደምናገኝ እንዴት እርግጠኞች እንሆናለን? ሉቃስ 12:11፣ 12
“አሁን፣ ከመጽሐፍ ቅዱሶቻችሁ ጋር በእግዚአብሔር ፊት ቅረቡ፣ በእግዚአብሔር ፊት ክፈቷቸው፣ እና እግዚአብሔርን ለምኑ። ግንዛቤህ እንዲነቃቃ ፈልግ፤ የእውነትን ትክክለኛ መርሆች እንደምታውቅ ለማወቅ ፈልግ ፣ ከዚያም ከተቃዋሚዎች ጋር ስትገናኝ የሚታገኛቸው በራስህ ጥንካሬ አይሆንም። ለሚጠየቁህ ጥያቄዎች ሁሉ መልስ ለመስጠት የእግዚአብሔር መልአክ ከጎንህ ይቆማል። ነገር ግን በዚያን ጊዜ ሰይጣን ተቃዋሚዎችህ ለአንተ ለመመለስ የሚከብድ ነገርን እንዲናገሩ ያስነሣሣቸው ዘንድ፥ አንተም ደግሞ ያለ ምክር እንድትናገር ለማድረግ ያነሳሳችኋል። ነገር ግን ንግግርህ ሰይጣን ከአንደበትህ በሚወጣው ቃልህ ሊጠቀምበት እንዳይችል የሚያደርግ ይሁን።”—The Review and Herald, May 3, 1887.
ማክሰኞ
፣ ግንቦት 26
3. በገዛ ፈቃዳቸው በታወሩት ፊት በድፍረት መናገር
ሀ. ፈሪሳውያን ዓይኑ የበራለትን ወጣት ማታለል ባለመቻላቸው እሱን እንዴት ናቁት—እንዲህ ያለው ድንቁርና በታሪክ ዘመናት የታየው እንዴት ነው? ዮሐንስ 9:28፣ 29፤ 1ኛ ቆሮንቶስ 1:18፣ 19፣ 26–28
“እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያኑ በእያንዳንዱ ትውልድ ልዩ እውነትና ልዩ ሥራ አለው። ከዓለማዊ ጥበበኛና አስተዋይ የተሰወረው እውነት እንደሕፃን ለሆኑ ለትሑታን ይገለጣል። የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግን ይጠይቃል። ይህንን ለማግኘት መታገል እና ማሸነፍ ያሉብን ድሎች አሉ። ስለእውነት ተሟጋቾች ጥቂት ናቸው፡፡ በዓለም ታላላቅ ሰዎች እና ከዓለም ጋር አንድ በሆኑ ቤተ ክርስቲያን ተቃውሞ እና ንቀትም ይገጥማቸዋል። . . .
“በዚህ ትውልድ ውስጥ ያሉ ታላላቅ የሀይማኖት መሪዎች ከዘመናት በፊት የእውነትን ዘር የዘሩትን ሰዎች በማወደስ ሀውልት ገነቡላቸው። ዛሬ ከዛው ዘር የሚወጣውን ችግኝ እድገት ለማቆምና ለመርገጥ ብዙዎች ፊታቸውን አያዞሩምን? እንዲህ የሚለው ያ የቀድሞ ጩኸት እየተደገመ ነው፣ 'እኛ እግዚአብሔር ሙሴን እንደ ተናገረው እንውቃለን፤ ይህ ሰው [ክርስቶስ] ግን ከወዴት እንደ ሆነ አናውቅም። ዮሐንስ 9፡29 ቀደም ባሉት ዘመናት እንደነበረው ሁሉ በዚህ ጊዜ ያሉት ልዩ እውነቶች የሚገኙት በቤተ ክርስቲያኒቱ ባለ ሥልጣናት ሳይሆን በጣም ያልተማሩ ወይም የአምላክን ቃል ለማመን ጥበበኞች ካልሆኑ ወንዶችና ሴቶች ጋር ነው።”—Christ’s Object Lessons, pp. 78, 79
ለ. ከወጣቱ እውነተኛ ምስክርነት እና ከሌሎች የክርስቶስ ታማኝ አማኞች ምን ምሳሌ እንማራለን? ዮሐንስ 9:30–33፤ የሐዋ. ሥራ 4:19፣ 20
“በጭምትነት ሁሉ፣ በጸጋ መንፈስ እና በእግዚአብሔር ፍቅር ጌታ እግዚአብሔር የሰማይና የምድር ፈጣሪ መሆኑን እና ሰባተኛው ቀን የጌታ ሰንበት መሆኑን ለሰዎች ልንጠቁም (ልንናገር) ይገባናል።
“በጌታ ስም፣ ባንዲራውን እያውለበልብን ቃሉን እየሰበክንወደ ፊት እንሂድ፡፡ ባለ ሥልጣናቱ ይህን እንዳናደርግ ሲያዝዙን፣ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት እና የየሱስን ኃይማኖት እንዳንሰብክ ሲከለክሉን፣ ያን ጊዜ እንደ ሐዋርያት “እግዚአብሔርን ከመስማት ይልቅ እናንተን እንሰማ ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት የሚገባ እንደ ሆነ ቍረጡ፤ እኛስ ያየነውንና የሰማነውን ከመናገር ዝም ማለት አንችልም” እንላቸዋለን። የሐዋርያት ሥራ 4:19፣ 20 —Testimonies for the Church, vol. 6, p. 395.
ረቡዕ
፣ ግንቦት 27
4. የጨለማ ባህሪያት፣ የጨለማ ድርጊቶች
ሀ. የተበሳጩት ፈሪሳውያን ማስረጃውን ለመቀበል ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ስለ ፈውሱ የመሰከረውን ወጣት ምን አደረጉ? ዮሐንስ 9፡34
“ሰውየው መርማሪዎቹን እንዳመጣጣቸው ተጋፈጣቸው። የአስተሳሰብ ስልቱን መቋቋም አልተቻለም። ፈሪሳውያኑ እንደ ጦር በሚወጋውና ቁርጠኛ በሆነው አነጋገሩ ተገርመውና ፈዝዘው ዝም አሉ። በዚህ ጊዜ የተበሳጩት ካህናትና የሕግ ምሑራን ከእርሱ ጋር በመነካካት እንረክሳለን ብለው የፈሩ በመምሰል ቀሚሶቻቸውን ሰብሰብ አደረጉና የእግሮቻቸውን አቧራ በማራገፍ “ሁለንተናህ በኃጢአት ተወርሶ የተወለድህ! አንተ እኛን ልታስተምር ነውን?» በማለት አሳጡትና አወገዙት።”—The Desire of Ages, p. 474.
ለ. በአንጻሩ የሱስ ወጣቱን የያዘው አያያዝ እንዴት ነበር? ዮሐንስ 9፡35-38
“ሰውየው በክርስቶስ እግር ሥር ወድቆ ሰገደለት። ሰውየው ያገኘው ፈውስ ለሥጋዊ ዓይኑ ብቻ ሳይሆን የማስተዋል ዓይኑም ተከፍቶለታል። ክርስቶስ ለነፍሱ ስለተገለጠለት ከእግዚአብሔር የተላከ መሆኑን አምኖ ተቀበለ።”—The Desire of Ages, p. 475.
ሐ. በተቃዋሚ አማፂያን እና እግዚአብሔርን በፍቅር የሚታዘዙትን ነፍሳት ከሚያሳድዱ ክርስቶስን ከሚቃወሙ እልከኞች መካከል ያለውን ትልቅ ልዩነት ያብራሩ። 1ኛ ነገሥት 9:6–9፤ ማቴዎስ 12:31፣ 32፤ መዝሙር 11:3
“[ዋይክሊፍ] የእግዚአብሔርን ኩነኔ በራሱ ላይ ካላመጣ በስተቀር ማንም ሰው ሊወገዝ እንደማይችል አስተማረ።”—The Great Controversy, p. 84.
በእነርሱ ዘመን መነገር ያለበትን፣ ለዚያ ጊዜ አስፈላጊ የሆነውን የተለየ መልእክት እንዲናገሩ እግዚአብሔር የሚገለገልባቸው ሁሉ፣ ተቃውሞ ዕጣ ፈንታቸው ይሆናል። ለዚያ ጊዜ የተለየ አስፈላጊነት የነበረው ወቅታዊ እውነት በሉተር ዘመን ነበር፤ ለቤተ ክርስቲያንዋ ዛሬም ወቅታዊ እውነት አለ። … ለዚህ ዘመን ያለውን ወቅታዊ እውነት የሚያቀርቡ እነርሱ፣ ያለፉት የተሐድሶ አራማጆች ከነበራቸው ተቀባይነት የተሻለ ተቀባይነት እናገኛለን ብለው መጠበቅ የለባቸውም። በእውነትና በሐሰት፣ በክርስቶስና በሰይጣን መካከል ያለው ታላቁ ተቃርኖ(ተጋድሎ) የዚህ ዓለም ታሪክ ሊዘጋ በተቃረበ ቁጥር እየጨመረ የሚሄድ ነው።”—Ibid., pp. 143, 144.
ሐሙስ
፣ ግንቦት 28
5. በብርሃኑ የተባረከ VS. በብርሃኑ የተፈረደበት
ሀ. የሱስ ስለ ሥራው ውጤት ምን አለ? ዮሐንስ 9፡39
“ጥቂት ፈሪሳውያን በአቅራቢያው ስለነበሩ እነርሱን ባየ ጊዜ የሱስ በቃሉና በሥራው ምክንያት የሚከሰተው ልዩነት ትውስ ስላለው «የማያዩ እንዲያዩ፣ የሚያዩም እንዲታወሩ እኔ ወደዚህ ዓለም ለፍርድ መጥቼአለሁ» ሲል ተናገረ። ክርስቶስ የመጣው የታወሩ ዓይኖችን ለመክፈትና በጨለማ የሚኖሩ ብርሃን እንዲያገኙ ለማድረግ ነው። የሱስ የዓለም ብርሃን መሆኑን ተናግሯል፣ አሁን የሠራው ተአምር ስለ ተልዕኮው ይመሰክራል። ክርስቶስ መጀመሪያ በመጣ ጊዜ ያዩት ሰዎች ከዚያ በፊት ለዓለም ተገልጾ በማይታ ወቅ አኳኋን መለኮት የበለጠ ተሟልቶ ተገልጾላቸዋል። ስለ እግዚአብሔር የበለጠ ለማወቅ ምቹ ሁኔታ ተፈጠረላቸው። እግዚአብሔርን የበለጠ ለማወቅ ከተሰጣቸው እድል ጋር ፍርድ ተላለፈባቸው። ባሕርያቸው ተፈተነ፣ የመጨረሻ መዳረሻቸውም ተወሰነ።”—The Desire of Ages, p. 475.
ለ. ፈሪሳውያን ለክርስቶስ ቃላት ምን ምላሽ ሰጡ? ዮሐንስ 9፡40 የሱስ ሲነግራቸው፣ lዓይነ ስውርነታቸው የዳረጋቸውን ጥፋታቸውን እንዴት ገለጠላቸው? ዮሐንስ 9፡41
“ዓይነስውር የነበረው ሰው ሥጋዊና መንፈሳዊ ብርሃን እንዲያገኝ ያደረገው መለኮታዊ ኃይል ፈሪሳውያኑን ወደባሰ ጥቅጥቅ ጨለማ እንዲገቡ አደረጋቸው። ከአዳማጮቹ ጥቂቶቹ የሱስ የተናገረው እነርሱን የሚመለከታቸው ስለመሰላቸው «ታዲያ እኛም ዕውሮች መሆናችን ነውን?» ብለው ሲጠይቁት የሱስ «ዕውሮች ብትሆኑማ ኖሮ ኃጢአት ባልሆነባችሁም ነበር» ሲል መለሰላቸው። እግዚአብሔር እውነትን ለማየት እንዳትችሉ አድርጓችሁ ቢሆን ኖሮ አለማወቃችሁ ኃጢአት አይሆንባችሁም ነበር። «አሁን ግን እናያለን» ትላላችሁ። ማየት እንችላለን ብላችሁ ስለምታምኑ ብርሃን ለማግኘት የምትችሉበትን ብቸኛ መንገድ ችላ ትላላችሁ። ፍላጐታቸውን ለሚያውቁ ሁሉ ክርስቶስ ወሰን የሌለው እርዳታ ይዞላቸው መጥቷል። ፈሪሳውያን ፍላጐት አለን ብለው ስላልተናዘዙና ወደ ክርስቶስ ለመምጣት ስላልፈለጉ እውር ሆነው ቀሩ፣ ለዚህም እውርነታቸው ኃላፊነቱ የራሳቸው ነው። ስለዚህ የሱስ «ኃጢአተኞች ሆናችሁ ትቀራላችሁ» አላቸው።—Ibid.
አርብ
፣ ግንቦት 29
የግል ግምገማ ጥያቄዎች
1. ፈሪሳውያን ዓይነ ስውር የነበረውን ሰው ለማሳመን የሞከሩት ነገር ምንድን ነው?
2. የማያምኑትን ፈሪሳውያን የሚጠቀምባቸው ማን ነበር?
3. ወጣቱ ግልጽና አሳማኝ መልስ እንዲሰጥ የረዳው ማን ነው?
4. እሱ በድፍረት ክርስቶስን ሲመሰክር ምን ሆነ?
5. ከሁሉ የከፋው የዓይነ ስውርነት ዓይነት ምን እንደሆነና ለምን እንደሆነ ግለጽ።