እሁድ
፣ ሰኔ 08
1. በቢታንያ ያለ ቤተሰብ
ሀ. የሱስ በቢታንያ ምን ዓይነት ደቀ መዛሙርት ነበሩት? ዮሐንስ 11፡5
“[የክርስቶስ] በቢታንያ ከሚገኝ አንድ ቤተሰብ ጋር ልቡ በጠንካራ የፍቅር ሰንሰለት ተያይዞ ስለነበር ከዚያ ቤተሰብ ለአንዱ በጣም አስደናቂ ድርጊት ፈጸመለት።
ብዙውን ጊዜ አዳኞችን በአልዓዛር ቤት እፎይታ ያገኝ ነበር። አዳኛችን የራሱ የሆነ ቤት ስላልነበረው በወዳጆቹና በደቀ መዛሙርቱ አስተናጋጅነት ይገለገል ነበር። ብዙውን ጊዜ ሰውነቱ በዛለና ከሰዎች ጋር ሆኖ መዝናናት ባስፈለገው ጊዜ ከእልኸኞቹ ፈሪሳውያን ቅናትና ጥርጣሬ ርቆ ሰላም ወደ ሰፈነበት ወደነአልዓዛር ቤት ጐራ ማለት ያስደስተው ነበር። በዚያ ቤት ውስጥ ልባዊ አቀባበል፣ ንጹህና የተቀደሰ ወዳጅነት ያገኝ ነበር። ንግግሩን እንደሚያስተውሉና በልባቸውም እንደሚቀበሉት በማወቅ በቀላል አነጋገርና ፍጹም በሆነ ነጻነት ይጫወታል።”—The Desire of Ages, p. 524.
ለ. እግዚአብሔር በምን ዓይነት ቤት ውስጥ ነው ከምርጥ በረከቶች የሚገኘው? ምሳሌ 3፡33 (የመጨረሻው ክፍል)።
“አዳኛችን አደብ የገዛ ቤተሰብንና መስማት የሚፈልጉ አዳማጮችን ይወድዳል። ሁል ጊዜ ሰብአዊ ርህራሄን፣ አክብሮትንና ፍቅርን ለማግኘት ናፍቆት ነበረው። እርሱ ለማካፈል ሁል ጊዜ ዝግጁ የሆነበትን ሰማያዊ ትምህ ርት የተቀበሉ ሁሉ ከፍተኛ በረከት አግኝተዋል።”—Ibid.
ሰኞ
፣ ሰኔ 09
2. አልዓዛር ታመመ
ሀ. የአልዓዛር እህቶች ወንድማቸው በጠና ሲታመም ምን እርምጃ ወሰዱ? ምን ምላሽስ አገኙ? ዮሐንስ 11፡1-4
“የሱስ በሚያርፍበት ሰላማዊ ቤት ውስጥ ሐዘን ገባ። አልዓዛር በድንገት ስለታመመ እህቶቹ «ጌታ ሆይ! ወዳጅህ ታሞአል» የሚል መልእክት ወደ የሱስ ላኩ። እህቶቹ ወንድማቸውን የያዘው ሕመም ኃይለኛ መሆኑን ቢያዩም ክርስቶስ ማንኛውንም የደዌ ዓይነት ለመፈወስ የሚችል መሆኑን እንዳሳየ ያውቁ ነበር። የሐዘናቸው ተካፋይ እንደሚሆን ስላመኑ ፈጥኖ እንዲደርስ አስቸኳይ ጥያቄ ሳያቀርቡ «ወዳጅህ ታሞአል» የሚል በእርሱ መተማመናቸውን የሚገልጽ መልእክት ብቻ ላኩ። የሱስ መልእክታቸው እንደደረሰው አፋጣኝ መልስ እንደሚሰጥና በተቻለው ፍጥነት ወደ ቢታንያ እንደሚመጣ አመኑ።
“ከየሱስ መልእክት ለማግኘት በጉጉት ተጠባበቁ። የወንድማቸው እስትንፋስ እስካልተቋረጠች ድረስ የሱስ እንዲመጣላቸው እየጸለዩ ተጠባበቁ። ነገር ግን መልእክተኛው የሱስን ሳይዝ ብቻውን ተመልሶ መጣ። ሆኖም መልእክተኛው «ይህ ሕመም ለሞት የሚያደርስ አይደለም» የሚል መልእክት ስላመጣ እትማማቾቹ አልዓዛር ከሞት ይተርፋል የሚል ተስፋ አደረባቸው። ስለሆነም ሕሊናውን በመሳት ላይ ለነበረው ሕመምተኛ በለሰለሰ አንደበት የተስፋ ቃል ለመናገር ሞከሩ።”—The Desire of Ages, pp. 525, 526.
ለ. በቀጣዮቹ ጥቂት ቀናት የነበሩትን የክርስቶስን ቃላት እና ድርጊቶች ግለጽ። ዮሐንስ 11፡5-8
“የሱስ በሁለቱ ቀናት ውስጥ ስለ አልዓዛር ምንም ነገር ባለመናገሩ የመጣለትን መልእክት ፈጽሞ የዘነጋው ይመስል ነበር። በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ የየሱስ መንገድ ጠራጊ የነበረው የዮሐንስ መጥምቁ ነገር ትዝ አላቸው። ታላላቅ ተአምራት የመሥራት ኃይል እያለው የሱስ ለምን ዮሐንስ በእስር ቤት እንዲማቅቅና በአሰቃቂ ሁኔታ እንዲሞት እንደፈቀደ ገረማቸው። ይህ ዓይነት ኃይል እያለው የሱስ ለምን የዮሐንስን ሕይወት አላዳነም? ፈሪሳውያን ይህን ጥያቄ የሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ላለመሆኑ መልስ የማይገኝለት የመከራከሪያ ነጥብ አድርገው ያቀርቡ ነበር። አዳኛችን ደቀ መዛሙርቱን ስለፈተና፣ ጉዳትና ስደት አስጠንቅቋቸዋል። ፈተና ሲደርስባቸው ችላ ይላቸው ይሆን? አንዳንዶቹ ተልዕኮው አልገባን ይሆን ብለው ተጠራጠሩ። ሁሉንም ጭንቀት ያዛቸው። …
“ደቀ መዛሙርቱ የሱስ ወደ ይሁዳ መሔዱ የማይቀር ከሆነ ለምን ሁለት ቀን ቆየ የሚል ጥያቄ አነሱ። በዚያ ወቅት ከፍተኛ ጭንቀት የፈጠረባቸው የክርስቶስና የራሳቸው ደህንነት ጉዳይነበር። የሱስ ያሰበው ጉዞ አደጋ ከማስከተል በቀር ሌላ ጥቅም እንደማያመጣ ስለተሰማቸው።”—Ibid., pp. 526, 527.
ማክሰኞ
፣ ሰኔ 10
3. ተስፋ መቁረጥ ወደ ተስፋ ተለወጠ
ሀ. ክርስቶስ በአልዓዛር ሕመም ዙሪያ የተፈጸሙትን ውስብስብ ክስተቶች እንዴት እንደያዘ በሚያሳየው ጊዜ ከማይሽረው መልእክት ምን እናገኛለን? ዮሐንስ 11:9፣ 10
“ከክርስቶስ ጋር ተባባሪዎች ሊሆኑ የሚችሉ፣ ነገር ግን መልእክተኞቹን እና መልእክታቸውን የናቁ ሁሉ፣ ያላቸውንም ያጣሉ። የሚሰናከሉበትን ሳያውቁ በጨለማ ይጓዛሉ። እነዚህ ሰዎች በመጨረሻዎቹ ቀናት ሽንገላ ለመታለል ዝግጁ ናቸው። አእምሯቸው በጥቃቅን ጉዳዮች የተጠመደ ሲሆን ከክርስቶስ ጋር የመተሳሰርና ከአምላክ ጋር አብረው የሚሠሩ ሠራተኞች የመሆንን የተባረከ አጋጣሚ ያጣሉ።”— Fundamentals of Christian Education, p. 471.
ለ. የሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ምን አስደናቂ መገለጥ እየሰጣቸው ነበር—ነገር ግን እነሱ ቃሉን እንዴት ተረዱ? ዮሐንስ 11:11፣ 12
“«የሱስ ይህን ካላቸው በኋላ ወዳጃችን አልዓዛር አንቀላፍቶአል፣ እኔ ግን ከእንቅልፉ ላስነሣው እሄዳለሁ» አለ። «ወዳጃችን አልዓዛርአንቀላፍቶአል» የሚለው አነጋገር ልብን የሚነካና ርህራሄ የተሞላበት ነው። ደቀ መዛሙርቱ ጌታቸው ወደ ኢየሩሳሌም በመሔድ ስለሚደርስበት አደጋ እየተጨነቁ ስለነበር በቢታንያ በሐዘን ላይ የነበሩትን ቤተሰብ ረሱዋቸው። ክርስቶስ ግን አልረሳቸውም። ይህ ለደቀ መዛሙርቱ ግሳጼ ነበር። አልዓዛርስለመታመሙ መልእክት እንደደረሰው የሱስ ወዲያውኑ አንድ ነገርአለማድረጉ ደቀ መዛሙርቱን ቅር አሰኝቷቸው ነበር። እነርሱ የገመቱትን ያህል የሱስ አልዓዛርንና እህቶቹን ቢወዳቸው ኖሮ ወዲያውኑ ከመልእክተኛው ጋር ይሔድ አልነበረምን የሚል ጥርጣሬ አድሮባቸው ነበር። ነገር ግን «ወዳጃችን አልዓዛር አንቀላፍቶአል» የሚለው አነጋገርአስተሳሰባቸውን እንዲያስተካክሉ አደረጋቸው። ክርስቶስ በስቃይ ላይየነበሩትን ወዳጆቹን እንዳልረሳቸው አመኑ።”—The De¬sire of Ages, p. 527.
ሐ. በትክክል የክርስቶስ ቃላት ምን ለማለት እንደነበረ ግለጽ። ዮሐንስ 11:13፣ 14
“የሱስ ለአማኝ ልጆቹ ሞትን በእንቅልፍ ይመስልላቸዋል። የሞቱት አማኝ ልጆቹ በእግዚአብሔር ዘንድ ሕይወታቸው በክርስቶስ ተከልሎ የመጨረሻው መለከት እስኪነፋ ድረስ በእርሱ እንዳንቀላፉ ይቆያሉ።”—Ibid.
ረቡዕ
፣ ሰኔ 11
4. መጠበቅ ፣ መጠበቅ ፣ መጠባበቅ
ሀ. የሱስ አልዓዛር መሞቱን ካወቀ በኋላም ወደ ቢታንያ ሳይመጣ የቆየው ለምንድን ነው? ዮሐንስ 11፡15
“ደቀ መዛሙርቱ ክርስቶስ «አልዓዛር ሞቶአል… እዚያ ባለመኖሬ...ደስ ብሎኛል» በማለቱ ተገረሙ። አዳኛችን እያወቀ ጉዳት ወደ ደረሰባቸው ወዳጆቹ ቤት ላለመሔድ ወሰነ? ማርታ፣ ማርያምና ሟቹ አልዓዛርብቻቸውን የተተው ይመስል ነበር። ነገር ግን ጠቅላላ ሁኔታው በክርስቶስ ቁጥጥር ሥር ስለነበረና አልዓዛር ከሞተ በኋላም ወንድማቸው የሞተባቸው እህትማማቾች በክርስቶስ ጸጋ ስለተጽናኑ ብቻቸውን አልነበሩም። ወንድማቸው ኃይለኛ ጠላቱ ከሆነው ከሞት ጋር በሚታገልበት ጊዜ የሱስ የእህትማማቾቹን በሐዘን የተጐዳ ልብ ተመልከቷል። ጌታ የሱስ ለደቀ መዛሙርቱ «አልዓዛር ሞቶአል» ባላቸው ጊዜ ሐዘንና ጭንቀት ተሰማው። ክርስቶስ በቢታንያ ስለነበሩት ወዳጆቹ ብቻ ሳይሆን ስለ ደቀ መዛሙርቱም ስልጠና ጭምር ያስብ ነበር። የአብን በረከት ለሁሉ ለማዳረስ እነዚህ ደቀ መዛሙርት በዚች ምድር ላይ የእርሱ ተወካዮች መሆን ነበረባቸው። ለእነርሱ ሲል አልዓዛር እንዲሞት ፈቀደ። ገና ሳይሞት ከሕመሙ ፈውሶት ቢሆን ኖሮ የመለኮታዊ ባሕርዩ ዋና መስረጃ የሆነው ተአምር አይታይም ነበር።”—The Desire of Ages, p. 528.
ለ. ታላቁ ፈዋሽ ወዳጁ አልዓዛርን በጠና ታሞ እንዲሞት ከፈቀደበት ሁኔታ ማስተዋል ያለብን ምንድነው? 1ኛ ቆሮንቶስ 15:17–19፤ መዝሙር 18:28
“[የክርስቶስ] ሥራ በበሽታ ላይ ኃይሉን በማሳየት አልቆመም። እያንዳንዱን የፈውስ ሥራ የፍቅሩንና የቸርነቱን መለኮታዊ መመሪያዎች በልብ ውስጥ የመትከል አጋጣሚ አድርጎታል።”—Counsels on Health, p. 249.
“ክርስቶስ አልዓዛር ታሞ በተኛበት ክፍል ውስጥ ቢኖር ኖሮ ሰይጣን ኃይል ስለማይኖረው አልዓዛር አይሞትም ነበር። ሕይወት ሰጭ የሆነው ጌታ በሚገኝበት ቦታ ሞት ቀስቱን በአልዓዛር ላይ ማነጣጠር አይችልም። ስለዚህ ክርስቶስ ከቦታው ርቆ ቆየ። ሰይጣንን የተሸነፈ ጠላት ኣድርጐ ለማባረርበማሰብ ኃይሉን እንዲያሳይ ፈቀደለት። ስለዚህ አልዓዛር በሞት ግዛት ሥርእንዲወድቅ ፈቀደ፣ ያዘኑት እህቶቹም ወንድማቸው በመቃብር ውስጥ ሲጋደም ተመለከቱ። ሁለቱ ሴቶች የሞተውን ወንድማቸውን ፊት ሲመለከቱ በአዳኛቸው ላይ የነበራቸው እምነት በከባድ ፈተና ላይ እንደሚወድቅ የሱስ ያውቅ ነበር። ነገር ግን አሁን በሚያደርጉት ትግል ምክንያት ሃይማኖታቸው የበለጠ ኃይል እንደሚያገኝ ያውቅ ነበር። እርሱም የሐዘናቸው ተካፋይ ነበር። በመዘግየቱ ለእነርሱ የነበረው ፍቅርኣልተቀነሰም። ለእነርሱ፣ ለአልዓዛር፣ ለራሱና ለደቀ መዛሙርቱ አንድ ድል እንደተዘጋጀላቸው ያውቅ ነበር።”—The Desire of Ages, p. 528.
ሐሙስ
፣ ሰኔ 12
5. ሁልጊዜ እንደጠበቅነው አይሆንም . . .
ሀ. የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች ሞት ምንም ይሁን ምን ምንጊዜም ምን ግምት ውስጥ ማስገባት አለብን? መዝሙር 116:15 ለዚህ አንድ ምሳሌ ጥቀስ።
“ኤልሳዕ ጌታውን በእሳት ሠረገላ አልተከተለም። ጌታ ለብዙ ጊዜ እንዲታመም ፈቀደ። በድካሙና በስቃዩ ጊዜ እንኳ እምነቱ እንደ ፀና ቆየ። የእግዚአብሔርን ተስፋ አጥብቆ ያዘ። መጽናናትንና ሰላምን የሰማይ መልዕክተኞች አመጡለት። . . . በእግዚአብሔር ላይ ያለው እምነት እየበረታ ሄደ። ሞት ጥሪውን ሲያሰማ ከሥራው ለማረፍ ዝግጁ ነበር።”—Prophets and Kings, pp. 263, 264.
ለ. የሱስ ከመምጣቱ በፊት በቢታንያ ምን ነገሮች ተከናውነዋል? የሱስ ሲደርስ ሌላ ማን እዚያ ነበር? ዮሐንስ 11፡17-19
“ክርስቶስ ወደ አልዓዛር ፈጥኖ ያልሔደበት ሌላው ምክንያት በእርሱ ለማያምኑት ሰዎች በመራራት ነው። የዘገየበት ምክንያት አልዓዛርን ከሞት በማስነሳት ልበ ደንዳናና ተጠራጣሪ ለሆኑት ሰዎች እርሱ «ትንሣኤና ሕይወት» መሆኑን እንዲያውቁ ሌላ እድል ለመስጠት ነበር። የሱስ ከእሥራኤል ቤት ተለይተው እንደ ጠፉ በጐች ስለሚንከራተቱት ምስኪን ሰዎች ገና ተስፋ አልቆረጠም ነበር። የሱስ እነዚህ ሰዎች ንስሐ ባለመግባታ ቸው ልቡ ተጨነቀ። የተበላሸውን የሚያድስ፣ ሕይወትንና ዘላለማዊነትን የሚሰጥ እርሱ ብቻ መሆኑን እንዲያውቁ በምህረቱ አንድ ተጨማሪ ማስረጃ ሊሰጣቸው አሰበ። ይህ ማስረጃ ካህናቱ አጣምመው ሊተረጉሙት የማይችሉ ነበር። ይህ ነበር የሱስን ወደ ቢታንያ ከመሔድ እንዲዘገይያደረገው። ይህ አልዓዛርን ከሞት የማስነሳት የተአምር ሁሉ ተአምር የሱስ ስለ ሥራው የእግዚአብሔር ሙሉ ድጋፍ እንዳለው የታየበትና መለኮታዊነቱንም ያስመሰከረበት ተአምር ነው።”—The Desire of Ages, p. 529.
አርብ
፣ ሰኔ 13
የግል ግምገማ ጥያቄዎች
1. የአልዓዛር ቤተሰብ አባላት እነማን ነበሩ?
2. የሱስ የወዳጆቹን ጥያቄ ወዲያውኑ ያልፈጸመው ለምንድን ነው?
3. ደቀ መዛሙርቱ ለክርስቶስ አመለካከት ምን ምላሽ ሰጡ?
4. የክርስቶስ አማኞች ሞትን እንዴት ሊመለከቱት ይገባል?
5. ክርስቶስ አልዓዛር እንዲሞት የፈቀደው ለምን ዓላማ ነው?