እሁድ
፣ ሰኔ 01
1. ሌባ እና እረኛው
ሀ. የሱስ በሌባውና በእረኛው መካከል ያለውን ልዩነት የገለጸው እንዴት ነው? በዚህስ ምን መንፈሳዊ ትምህርት እየሰጠ ነው? ዮሐንስ 10:1፣ 2
“ክርስቶስ እነዚህ ትንቢቶች [በኢሳይያስ 40:9–11፤ መዝሙር 23:1፣ እና ሕዝቅኤል 34:23፣ 16፣ 25፣ 28] ስለ እርሱ የተነገሩ መሆኑን በመግለጽ በእርሱ ባሕርይና በእሥራኤል መሪዎች ባሕርይ መካከል ያለውን ልዩነት አሳየ። ከጥቂት ጊዜ በፊት ፈሪሳውያን አንድ አባል ስለ ክርስቶስ ኃይል ለመመስከር ስለ ደፈረ ከመንጋው ለይተው አባርረውታል። እውነተኛው እረኛ ወደ እርሱ እየሳበው የነበረውን ነፍስ ከመንጋው ለይተውታል። ይህን በማድረጋቸው የተሰጣቸውን ሥራ እንዳላወቁና የመንጋው እረኛ ለመሆንም ብቃት እንደሌላቸው አሳዩ! ስለዚህ የሱስ በእነርሱና በመልካሙ እረኛ መካከል ያለውን ልዩነት በማሳየት እርሱ የእግዚአብሔር መንጋ እውነተኛ ጠባቂ መሆኑን ገለጸ።”—The Desire of Ages, p. 477.
“ረዳት አልባና በእርሱ ጥገኛ ስለሆንን ክርስቶስ ይወደናል።”—Sermons and Talks, vol. 1, p. 248..
ለ. በበጎቹና በእረኛቸው መካከል ምን ዝምድና አለ? ዮሐንስ 10:3፣ 4 በጎቹ በእንግዳ ፊት ምን ያደርጋሉ? ዮሐንስ 10፡5
ሰኞ
፣ ሰኔ 02
2. የመንጋው በር
ሀ. የሱስ ከፈሪሳውያን ጋር ያለውን ልዩነት የገለጠው እንዴት ነው? ዮሐንስ 10፡7-10
“ክርስቶስ ወደ እግዚአብሔር መንጋ መግቢያ በር ነው። ከጥንት ጀምሮ ልጆቹ የሆኑት ሁሉ የገቡት በዚህ በር ነው እነዚህ ልጆቹ በምሳሌነት በቀረቡት መስዋዕቶች፣ ለነቢያት በተገለጹት ራእዮች፣ ለደቀ መዛሙርቱ ባስተማራቸው ትምህርቶችና ለሰው ልጆች በሠራቸው ተአምራት የሱስ «የእግዚአብሔር በግ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ» መሆኑን ለማየት በቅተዋል፣ በእርሱም ከጸጋው መንጋ ጋር ለመቀላቀል ችለዋል። ብዙዎች ለዓለም ሃይማኖት ሌላ ዓላማ ይዘው ተነስተዋል፣ እንደዚሁም ሰዎች . ከእግዚአብሔር ይቅርታና ሰላም ለማግኘትና ከመንጋው ጋር ለመቀላቀል ይችሉ ዘንድ አገልግሎቶችንና ሥርዓቶችን ቀይሰዋል። ብቸኛው በርክርስቶስ ነው። በክርስቶስ ምትክ ሌላ ነገር የሚያስገቡ ወይም በሌላ መንገድ ወደ መንጋው ለመግባት የሚሞክሩ ሁሉ ሌቦችና ወንበዴዎች ናቸው።
“ፈሪሳውያኑ በዚህ በር በኩል አልገቡም። ወደ መንጋው የገቡት በክርስቶስ በኩል ሳይሆን በሌላ በኩል ተንጠላጥለው ስለሆነ የእውነተኛውን እረኛ ተግባር አልፈጸሙም። ካሕናቱ፣ ሹማምንቱ፣ ጸሐፍቱና ፈሪሳውያን የበጐቹን መሰማሪያ ቦታ አጠፉት፣ የሕይወት ውሃ ምንጩንም በከሉት። የመንፈስ ቃል እነዚህን የሐሰት እረኞች «ለደከሙት ክብካቤ አላደረጋ ችሁላቸውም፣ የታመሙትንም አላዳናችሁም፣ የተሰበሩትን አልጠገናች ሁም፣ የባዘኑትን አልመለሳችሁም፣ የጠፉትን አልፈለጋችሁም፣ ይህን በማድረግ ፈንታ በግፍና በጭካኔ ገዛችኋቸው» በማለት ምንነታቸውን በትክክል ገልጾታል። ሕዝ. 34:4”—The Desire of Ages, pp. 477, 478.
ለ. እውነተኛው እረኛ ከተቀጣሪ የሚለየው እንዴት ነው? ዮሐንስ 10፡11-13
“በቃል የሚያስተምሩ ብቻ ሳይሆኑ በተግባራቸው እውነትን ለሌሎች የሚገልጡ ሰዎች ያስፈልጋሉ፡፡ የክርስቶስ አገልጋይ መሆን የሚያኮራቸውና ተሸከሙ ያላቸውን መስቀል መሸከም የተማሩ ሰዎች በብዛት ይፈለጋሉ፡፡
አንድ ቄስ (ወንጌላዊ) የሚያገለግላቸውን ሰዎች በቅርብ ማወቁ ይጠቅመዋል፡፡ በቀላሉ ሊያስተምራቸው አንዲችል አስተሳሰባቸውን ማወቅ አለበት፡፡ ያን ጊዜ ተፈጥሮንና ሰዎችን በቅርብ ለሚከታተሉ ሰዎች የሚሰጠው የማስተዋል ጸጋ ይሰጠዋል።”—Gospel Work¬ers, p. 191.
ማክሰኞ
፣ ሰኔ 03
3. የተለመደው መልካም እረኛ
ሀ. የሱስ የገለጠው ሌላኛው የመልካም እረኛ ባሕርይ ምንድነው? ዮሐንስ 10:14፣ 15
“ዓለማዊ የበግ እረኛ በጐቹን እንደሚያውቅ ሁሉ እንዲሁም መለኮታዊዩ እረኛ በዓለም ላይ ተበታትነው የሚገኙትን በጐቹን ያውቃቸዋል። «በበጐች የተመሰላችሁትና እኔ የምመግባችሁ መንጋ እናንተ የእሥራኤል ሕዝብ ናችሁ። አኔም አምላካችሁ ነኝ።» የሱስ «አንተ የእኔ ነህ፣ በስምህም ጠርቼሃ ለሁ» ይላል። «ስምሽን በእጄ መዳፍ ላይ ጽፌዋለሁ።» ሕዝ.34:31፤ ኢሳይያስ 43:1፤ 49:16።
የሱስ እያንዳንዳችንን ያውቀናል፣ በድካማችንም ይራራልናል። ሁላችንንም በስም ያውቀናል። የምንኖርበትን ቤትና በውስጡም የሚኖሩትን ሁሉ ያውቃል። አንዳንድ ጊዜ ከበጐቹ አንዱን ለመገናኘት አገልጋዮቹን ወደ እንደዚህ ያለ ከተማ፣ ወደ እንደዚህ ያለ መንገድና ወደ እንደዚህ ያለ ቤት ሒዱ ብሎ አዞአል።
እያንዳንዱ ነፍስ ክርስቶስ ለእርሱ ብቻ የሞተለትን ያህል ይታወቃል። የእያንዳንዱ ሰው ስቃይ የየሱስን ልብ ይነካል። እርዳታ ለማግኘት የሚደረግ ጩኸት ሁሉ ወደ ጆሮው ይደርሳል። እርሱ የመጣው ሰዎችን ሁሉ ወደ እርሱ ለመሳብ ነው። እርሱ «ተከተሉኝ» እያለ ይጠራል፤ ሰዎች ወደ እርሱ እንዲሳቡ ለማድረግ መንፈሱ ልባቸውን ይቀሰቅሳል። ብዙዎች ለመከተል ፈቃደኛ አይደሉም። የሱስ እነርሱንም ያውቃቸዋል። ጥሪውን በደስታ ተቀብለው ወደ እርሱ ጥበቃ ሥር የሚመጡትንም ያውቃቸዋል። «እኔ በጐቼን አውቃለሁ! በጐቼም እኔን ያውቁኛል» ይላል። በዓለም ላይ ሌላ በግ እንደ ሌለ ያህል እርሱ ለእያንዳንዱ በግ ይጠነቀቃል።”—The Desire of Ages, pp. 479, 480.
ለ. የሱስ ያሰበላቸው ለሌሎቹ ለየትኞቹ በጎች ነው? ዮሐንስ 10፡16
“የሱስ በዓለም ስላሉት በሐሳዊ እረኞች ስለተሳሳቱት ነፍሳት አሰበ። ከበጐቹ ጋር ሊቀላቅላቸው የፈለገው በጐች በተኩላዎች መካከል ተበታት ነው ይገኙ ስለነበር፣ «በዚህ መንጋ ውስጥ ያልሆኑ ሌሎች በጐች አሉኝ፡ እነርሱንም ማምጣት ይገባኛል! እነርሱ ድምጼን ይሰማሉ፣ አንድ መንጋም ይሆናሉ፣ እረኛውም አንድ ይሆናል፣» ሲል ተናገረ። ዮሐ.10:16።”—Ibid., p. 483.
“እግዚአብሔር በአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ውስጥ ዕንቁዎች አሉት፣ እኛ ሃይማኖተኞች ነን በሚሉት ዓለም ላይ ሰፊ ውግዘት ልንሰጥ አይገባንም፤ ነገር ግን እውነት በትሕትናና በፍቅር በየሱስ እንዳለ ሁሉ እንዲሁ አቅርቡላቸው። ሰዎች በእኛ ውስጥ እግዚአብሔርን መምሰልና መታመንን፣ እንዲሁም ክርስቶስን የሚመስሉ ባሕርያትን ይዩ፣ በዚያን ጊዜ ወደ እውነትም ይሳባሉና።”—The SDA Bible Commentary [E. G. White Comments], vol. 4, p. 1184.
ረቡዕ
፣ ሰኔ 04
4. መለኮታዊ ኃይል
ሀ. የሱስ ምን ዓይነት መለኮታዊ ኃይል እንዳለው ተናግሯል? ዮሐንስ 10:17፣ 18
“«እንደገና መልሼ የምወስዳትን ሕይወቴን አሳልፌ ለመስጠት ፈቃደኛ ስለሆንሁ አብ እኔን ይወድደኛል።» ይህም አባቴ እናንተን እጅግ ከመውደዱ የተነሳ እኔ እናንተን ለማዳን ሕይወቴን ስለሰጠሁ የበለጠ ወደደኝ ማለት ነው። ሕይወቴን አሳልፌ በመስጠት፣ የእናንተን እዳና በደል በመረከብ ቤዛችሁና አለኝታችሁ በመሆኔ በአባቴ ዘንድ ተወዳጅነትን እተረፍሁ።
«ሕይወቴን በፈቃዴ አሳልፌ እሰጣለሁ እንጂ ከእኔ የሚወስዳት ማንም የለም። ሕይወቴን አሳልፌ ለመስጠትና መልሼም ለመውሰድ መብት አለኝ።» የሰብአዊ ቤተሰብ አባል በመሆኑ ሟች ሆነ፣ አምላክ በመሆኑ ደግሞ ለዓለም የሕይወት ምንጭ ሆነ። ላለመሞትና በሞት ሥልጣን ሥርላለመግባት አሻፈረኝ ማለት ይችል ነበር። ነገር ግን ሕይወትንና አለሟች ነትን ለማስገኘት ሲል ሕይወቱን በፈቃዱ አሳልፎ ሰጠ። ሰዎች ለዘላለም ሞተው እንዳይቀሩ ሲል የዓለምን ኃጢአት ተሸከመ፣ እርግማንዋንም ተጋፈጠ፣ ሕይወቱንም ለመስዋዕትነት አሳልፎ ሰጠ። «እኛ ልንሸከመው የሚገባንን መከራና ሕማም እርሱ ተሸከመ። ይህ በእርሱ ላይ የደረሰበት ግርፋትና መከራ ሁሉ ከእግዚአብሔር የተላከ ቅጣት እንደሆነ አድርገን አሰብን። ይሁን እንጂ እርሱ ተወግቶ የቆሰለው ስለ ኃጢአታችን ሲሆን በመገረፍ የደቀቀውም ስለ ፈጸምነው በደል ነው። እርሱ በተቀበለው ቅጣት እኛ ሰላምን አገኘን። እርሱም በመቁሰሉ እኛ ተፈወስን። እኛ እያንዳንዳችን ከመንገድ ወጥተው በመባዘን እንደ ጠፉ በጐች ሆነን ነበር። ነገር ግን እግዚአብሔር እኛ ልንቀበለው የሚገባንን ቅጣት ሁሉ በእርሱ ላይ አኖረ።» ኢሳይያስ 53:4-6።”—The Desire of Ages, pp. 483, 484.
ለ. ሰዎች ክርስቶስን እንዲከተሉ የሚመራቸው ምንድን ነው? ዮሐንስ 10:27፤ 1ኛ ዮሐንስ 4:10፣ 19
“የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ክርስቶስን የሚከተሉት ቅጣት በመፍራት ወይም የዘላለም ዋጋ ለማግኘት በመመኘት አይደለም። እነርሱ ክርስቶስን የሚከተሉበት ምክንያት ክርስቶስ በዚህ ዓለም ላይ በእንግድነት ከቤተልሔም በረት እስከ ቀራንዮ መስቀል ድረስ በኖረ ጊዜ የተከሰተውን ወደር የሌለውን ፍቅሩን ስላዩና እርሱን ማየት ደግሞ ነፍስን ስለሚስብ፣ ስለሚያረጋጋና ትሑት እንዲሆን ስለሚያደርግ ነው። ፍቅር የተመልካቹን ልብ ያነቃቃል። ስለዚህ ድምጹን ሰምተው ይከተሉታል።”—Ibid., p. 480.
“በምድር ላይ ያለውን ህይወቱን፣ ለእኛ ሲል የከፈለውን መስዋዕትነት፣ በሰማይ አማላጃችን ሆኖ የሚሰራውን ስራውን እና ለሚወዱት የሚያዘጋጃቸውን መኖሪያ ቤቶች ስናሰላስል፣ የክርስቶስ ፍቅር እንዴት ያለ ታላቅ እና ጥልቅ ነው! በማለት እንደነቃለን፡፡”—The Acts of the Apostles, p. 334.
ሐሙስ
፣ ሰኔ 05
5. የመዳን ዋስትና
ሀ. የሱስ ለበጎቹ ምን ማረጋገጫ ሰጣቸው? ዮሐንስ 10:28፣ 29
ምንም እንኳን አሁን የሱስ እግዚአብሔር አብ ወዳለበት ቦታ ያረገና የዩኒቨርስን (የዓለማትን) ዙፋን ቢጋራም ቅሉ ርህሩህ ባሕርዩ አልተለየውም። ዛሬም ያው ደግና አዛኝ ልቡ የሰብአዊ ዘርን ሰቆቃ ለማስወገድ ክፍት ነው። ዛሬም በምስማር የተወጉት እጆቹ በዓለም የሚኖሩትን ሕዝቦቹን በበለጠ ለመባረክ ተዘርግተዋል። «እኔ የዘላለም ሕይወት እሰጣቸዋለሁ፣ ስለዚህ ከቶ አይጠፉም፣ ከእኔ እጅ ማንም ነጥቆ አይወስዳቸውም።»
ራስዋን ለክርስቶስ ያስረከበች ነፍስ በእርሱ ዘንድ ከመላው ዓለም የበለጠ የተከበረች ናት። ያችን አንዲት ነፍስ ለመንግሥቱ ለማዳን ሲል አዳኛችን የቀራንዮን ስቃይ መቀበሉ አይቀርም ነበር። የሞተላትን ነፍስ ፈጽሞ ችላ አይላትም። ተከታዮቹ ከእርሱ ተለይተው ለመሔድ ካልፈለጉ በስተቀር እርሱ አጥብቆ ይይዛቸዋል።”—The Desire of Ages, pp. 480–483.
ለ. የእኛ መንፈሳዊ ደህንነት እና የመዳን ዋስትና በምን ላይ ያርፋል? ሮሜ 8፡31-39
“በሰማዩ አደባባይ፣ ክርስቶስ ስለ ቤተክርስቲያኑና በደሙ ዋጋ ለከፈለላቸው ይማጸናል። ምዕተ-አመታት፣ ዘመናት፣ የእርሱን የኃጢያት ክፍያ መስዋዕትነት በፍፁም ሊቀንሱት አይችሉም። ሕይወትም ቢሆን ሞትም ከፍታም ቢሆን ዝቅታም በክርስቶስ የሱስ ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን አይችልም። ይህም የሆነው እርሱን አጥብቀን ስለያዝነው ሳይሆን እርሱ አጥብቆ ስለሚይዘን ነው። መዳናችን በራሳችን ጥረት ላይ የተመሰረተ ከሆነ መዳን አንችልም ነበር፤ ነገር ግን መዳናችን ከተስፋዎቹ ሁሉ ጀርባ ባለው አካል ላይ የተመካ ነው። እርሱን የያዝንበት አያያዛችን ደካማ ሊመስል ይችላል፣ ነገር ግን ፍቅሩ የታላቅ ወንድም ነው። ከእርሱ ጋር ያለንን አንድነት እስካጠናከርን ድረስ ማንም ከእጁ ሊነጥቀን አይችልም።”—The Acts of the Apostles, pp. 552, 553.
አርብ
፣ ሰኔ 06
የግል ግምገማ ጥያቄዎች
1. በእረኛና በሌባ መካከል ያለውን የምግባር ልዩነት ግለጽ።
2. የሱስ ራሱን የገለጸው በምን ሌላ ምሳሌ ነው?
3. እውነተኛ እረኞች ከበጎቻቸው ጋር ምን ያደርጋሉ?
4. በጎቹ እረኛውን እንጂ እንግዳ የማይከተሉት ለምንድን ነው?
5. ስለመዳናችን እንዴት እርግጠኞች መሆን እንዳለብን ግለጽ።