እሁድ
፣ ሚያዚያ 05
1. የየሱስ ሕይወት በቤት ውስጥ
ሀ. የሱስ በራሱ ቤት ውስጥ ምን ከባድ ፈተና አጋጥሞታል? ዮሐንስ 7፡5
“የሱስ ገና ከሕጻንነቱ ጀምሮ ስለ ጸባዩ አመሠራረት በግሉ መጣርጀመረ፤ ለወላጆቹ የነበረው አክብሮትና ፍቅር እንኳን ለእግዚአብሔር ከመታዘዝ ሊገታው አልቻለም። ከቤተሰብ ባሕልና ልማድ የተለየ ለሚያደርገው ድርጊት ሁሉ ማስረጃው «ተጽፎዋልና» የሚል ነበር። ነገርግን የምሑራኑ ተጽእኖ ኑሮውን የመረረ አደረገው። ገና በወጣትነቱ በእርጋታና በትዕግስት ችግርን የመቋቋም ከባድ ትምህርት መማር ነበረበት።
ወንድሞቹ ተብለው የሚጠሩት የዮሴፍ ልጆች ከምሑራኑ ጋር ተባበሩ። ባሕላዊ ደንቦች እንደ እግዚአብሔር ሕግ መከበር አለባቸው ባዮች ነበሩ። ሰው ሰራሽ ሕግጋትን ከእግዚአብሔር ቃል አብልጠው ያከብሩ ስለነበርየሱስ በእውነትና በሐሰት መካከል ያለውን ልዩነት ጠንቅቆ ማወቁ ያበሳጫቸው ነበር። የእግዚአብሔርን ሕግ በትክክል ስላከበረ በጽኑ አወገዙት። የምሑራኑን ጥያቄዎች በመመለስ ስላሳየው ዕውቀትና ጥበብ ተደነቁ። ከአዋቂዎቹ የቀሰመው ትምህርት አለመኖሩን ቢያውቁም ምሑራኑን ሊያስተምራቸው እንደሚችል ለመረዳት ተገደዱ። የእርሱ ዕውቀት ከእነርሱ ዕውቀት የላቀ መሆኑን ተገነዘቡ። ነገር ግን እነርሱ ከማያውቁት የዕውቀት ምንጭ ከሆነው ከሕይወት ዛፍ ጋር ግንኙነት እንደነበረው አላስተዋሉም።”—The Desire of Ages, p. 86.
ሰኞ
፣ ሚያዚያ 06
2. የዮሴፍ ልጆች
ሀ. የክርስቶስ ወንድሞች አመታዊውን የዳስ በዓል ጠብቀው ለእርሱ ምን ሐሳብ አቀረቡለት? ዮሐንስ 7:3፣ 4
“[የክርስቶስ] ወንድሞች የሱስ ምሑራኑን ማራቁ ስሕተት ነው ብለው ያምኑ ነበር። ወንድሞቹ ምሑራኑ ትክክል እንደሆኑና የሱስ ከእነርሱ ጋር ተቃውሞ መፍጠሩ ስሕተት ነው የሚል ስሜት ነበራቸው። ይሁን እንጂ ሕይወቱ እንከን እንዳልነበረበት አይተዋል፣ የደቀ መዛሙርቱን ያህል ባይሆንም በሠራው ሥራ ልባቸው በጣም ተነክቶ ነበር። በገሊላ ያገኘው ዝና ምኞታቸውን የሚያረካላቸው ስለመሰላቸው ተደሰቱ፣ ፈሪሳውያን የእርሱን ማንነት እንዲያውቁ ለማድረግ ኃይሉን ያሳያል የሚል ተስፋም ነበራቸው። መሲሑ ወይም የእሥራኤል መስፍን ቢሆንስ! ይህን ሐሳብ በኩራትና በደስታ ማሰላሰላቸው አልቀረም።
ስለዚህ ነገር እጅግ ከመጓጓታቸው የተነሳ የሱስ ወደ ኢየሩሳሌም እንዲሔድ ገፋፉት። «ከዚህ ውጣ፣ ወደ ይሁዳም ምድር ሒድ፣ ደቀ መዛ ሙርትህ ደግሞ የምትሰራትን ስራ ያዩ ዘንድ። ማንም በቀስታ (በምስጢር) ነገር የሚያደርገው የለምና እርሱም በግልጥ ይሆን ዘንድ ይወዳል። ይህንስ ማድረግ ትወድ እንደሆንህ ራስህን ለዓለም ኣሳይ፣» አሉት። «እንደ» የሚለው ቃል ጥርጣሬንና አለማመንን ያመለክታል። እርሱ ፍርሃትና ድክመት ያለበት መሰላቸው። መሲሕ መሆኑን ካወቀ ለምን ዝም ይላል? እውነትም ኃይል ካለው ለምን በድፍረት ወደ ኢየሩሳሌም ሔዶ ማንነቱን አያረጋግጥም? በገሊላ ፈጸማቸው የተባሉትን አስደናቂ ድርጊቶች ለምን በኢየሩሳሌም አይፈጽማቸውም? ባልታወቁ ቦታዎች ተደብቀህ አስገራሚውን ሥራህን ለምን ላልተማሩት ገበሬዎችና አሣ አጥማጆች ጥቅም ብቻ እንዲውል ታደረገዋለህ? አሉት። ወደ ርዕሠ ከተማው ሒድና የካህናቱንና የሹማምንቱን ድጋፍ በመያዝ አዲስ መንግሥት መስርተህ ሕዝቡን አስተባብር።”—The Desire of Ages, p. 450.
ለ. ሁልጊዜ የዋሆችን የሚያጋጠሟቸውን ችግር ግለጽ። መዝሙር 86:14
“እነዚህ የየሱስ ወንድሞች ያስቡ የነበሩት ልታይ ልታይ የሚል ምኞት ያላቸው ሰዎች እንደሚያስቡት ነው። ይህ መንፈስ በዓለም ላይ የሰፈነ ነበር። የሱስ ዓለማዊ መንግሥትን ከመመኘት ፈንታ የሕይወት እንጀራ ነኝ ማለቱ አስቀየማቸው። ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎቹ ትተውት ስለሔዱ በጣም አዘኑ። እርሱ ከእግዚአብሔር የተላከ ለመሆኑ ሥራው የሚመሰክርለት መሆኑን ላለመቀበል ሲሉ እነርሱ ራሳቸው ፊታቸውን ከእርሱ አዙረው ነበር።”—Ibid., p. 451.
ማክሰኞ
፣ ሚያዚያ 07
3. ስለየሱስ የተደረገ ክርክር
ሀ. ስለ የሱስ ምን ተቃራኒ አስተያየቶች ተነስተዋል? ዮሐንስ 7:11፣ 12
“የሱስ ስለሠራቸው ተአምራት ወሬው ከኢየሩሳሌም ተነስቶ አይሁዶች ተበታትነው ወደሚኖሩበት ቦታ ሁሉ ተናኝቶ ስለነበር ምንም እንኳን የሱስ ለብዙ ወራት በበዓላቱ ላይ ባይገኝም ሕዝቡ ስለ እርሱ የነበረው ስሜት አልቀነሰም ነበር። የዳሱን በዓል ለማክበር ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የመጡ ብዙ ሰዎች እርሱን ለማየት ተስፋ ነበራቸው። በዓሉ እንደተጀመረ ስለ እርሱ ብዙ ጥያቄዎች ተሰነዘሩ። ፈሪሳውያኑና ሹማምንቱ እርሱን ለማውገዝ ጥሩ አጋጣሚ እንዳገኙ በማሰብ ይፈልጉት ነበር። በጉጉት «የት ነው ያለ?» እያሉ ጠየቁ፣ ግን የሚያውቅ ሰው አልተገኘም። ሁሉም ስለ እርሱ ያስቡ ነበር። ካህናቱንና ሹማምንቱን በመፍራት የእርሱን መሲሕነት አምኖ ለመቀበል የደፈረ አይኑር እንጂ ብዙ ሰዎች በየቦታው ስለ እርሱ ከልባቸው ይነጋገሩ ነበር። ብዙዎቹ ከእግዚአብሔር የተላከ መሆኑን በመደገፍ ሲናገሩ ሌሎች ግን ሕዝብን አታላይ ነው እያሉ ተከራከሩ።”—The Desire of Ages, pp. 451, 452.
ለ. የሱስ ስለ ራሱ የሚናገሩትን ተቃራኒ አስተያየቶች እንዴት ነበር ዝም ያሰኘው? ዮሐንስ 7:14–18፤ ሉቃስ 4፡32።
“በበዓሉ አጋማሽ ላይ ስለ እርሱ የሕዝቡ ስሜት ከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሰበት ወቅት ሕዝቡ ከዚያ እያለ ወደ ቤተ መቅደሱ አደባባይ ገባ። ከዚያ በፊት በበዓሉ ላይ ስላልተገኘ በካህናቱና በሹማምንቱ እጅ ላለመግባት ስለፈራ ነው ተብሎ ተወርቶ ነበር። አሁን ግን ከዚያ በመገኘቱ ሁሉንም ገረማቸው። ሁሉም ጸጥ አሉ። ሕይወቱን ለማጥፋት በተጠሙት ብርቱ ጠላቶቹ መካከል በእርሱ ላይይታይበት በነበረው ክብርና ድፍረት ያልተደነቀ ሰው አልነበረም።
የሱስ በዚህ አኳኋን የዚያን ብዙ ሕዝብ ትኩረት እንደሳበ ቆሞ ከማንም አንደበት ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ ንግግር አደረገላቸው። በንግግሩ ስለ እሥራኤል ሕግጋትና ሥርዓቶች፣ ስለ መስዋዕት አገልግሎትና ስለ ነቢያት ትምህርት ከካህናቱና ከሊቃውንቱ በጣም የበለጠ እንደሚያውቅ ግልጽ ሆነ። የአባቶችን ወግና የሥርዓት አምልኮትን መሰናክል አፈራረሰው። የወደፊቱ ሕይወት ትዕይንት ግልጽ ሆኖ የሚታየው ይመስል ነበር። የማይታየውን ኣምላክ እንደሚያየው ሆኖ ስለ ዓለማዊና ሰማያዊ፣ ስለ ሰብአዊና መለኮታዊ ጉዳዮች በሙሉ ሥልጣን ተናገረ። አነጋገሩ ግልጽና አሳማኝ በመሆኑ በቅፍርናሆም እንደሆነው ሁሉ «በሥልጣን ቃል ይናገር ስለነበር፣» (ሉቃ.4:32) ሕዝቡ በትምህርቱ ተደነቁ። … ስለ ሕግና ትንቢቶች የነበረው እውቀት ሁሉንም ስላስገረማቸው።”—Ibid., pp. 452, 453.
ረቡዕ
፣ ሚያዚያ 08
4. በቅዱሱ ላይ ጥላቻ
ሀ. የሱስ በአይሁድ መሪዎች ውስጥ ምን ተገነዘበ እና ምን ጥያቄ አቀረበላቸው? ዮሐንስ 7፡19
ክርስቶስ በልባቸው ያስቡት የነበረውን በማወቅ ለአይሁድ ምሑራን ስለ መለኮታዊነቱ ምልክት አሳያቸው። እነዚህ ምሑራን የሱስ በቤተሳይዳ ከሰጠው የፈውስ አገልግሎት ጀምሮ ሕይወቱን ለማጥፋት ሲዶልቱ ቆይተዋል። ይህን በማድረጋቸው ሽንጣቸውን ገትረው ይከራከሩለት የነበረውን ሕግ ራሳቸው ጣሱት። ስለዚህ የሱስ «ሙሴ ሕግን ሰጥቶአችሁ የለምን? ነገር ግን ከእናንተ ሕግን የሚፈጽም ማንም የለም። እናንተ ለምን ልትገድሉኝ ትፈልጋላችሁ?» አላቸው።”—The Desire of Ages, p. 456.
ለ. ለክርስቶስ በሰጡት ምላሽ፣ የአይሁድ መሪዎች ስለ ምን ከሰሱት— እርሱስ በተራው ምን ምላሽ ሰጠ? ዮሐንስ 7፡20-23
“የሱስ ግን ይህን የአሽሙር ንግግር ከቁም ነገር ባለመቁጠር የቤተሳይዳው ፈውስ የሰንበትን ሕግ የማይጻረርና በአይሁዶች ሕግ አተረጓጐም መሠረትም ቢሆን ትክክል መሆኑን አብራራላቸው። ቀጥሎም «ሙሴ የግዝረ ትን ሥርዓት ሰጣችሁ...ታዲያ እናንተ በሰንበትም እኮ ሰውን ትገርዛላ ችሁ፣» አላቸው። በሕጉ መሠረት እያንዳንዱ ሕጻን በተወለደ በስምንተ ኛው ቀን መገረዝ ነበረበት። ይህ ስምንተኛ ቀን ሰንበት ቢሆንም የግዝረቱ ሥርዓት መካሔድ ነበረበት። «በሰንበት ቀን የሰውን ሁለንተና፣» መፈወስ ከሕጉ መንፈስ ጋር የበለጠ ተስማሚ መሆን ነበረበት አላቸው።—Ibid., pp. 456, 457.
ሐ. የክርስቶስ ቀጣይ ማስጠንቀቂያ የያዘውን ሰፊ ጠቀሜታ አብራራ። የዮሐንስ ወንጌል 7፡24
“ባለሥልጣኖቹ ዝም ኣሉ፣ ሕዝቡ ግን «ሊገድሉት የሚፈልጉት ሰው ይህ አይደለምን? እነሆ እርሱ በግልጥ ይናገራል፣ እነርሱም ምንም አላሉትም። ይህ ሰው መሲሕ መሆኑን ባለሥልጣኖች በእውነት ዐውቀው ይሆን?» ብለው ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ተናገሩ።”—Ibid., p. 457.
“[ክርስቶስ] ውጫዊውን ገጽታ አይመለከትም። እሱ ሰው እንደሚፈርድ አይፈርድም። ለሰው እንደ ደረጃው፣ እንደ ችሎታው፣ እንደ ትምህርቱ ወይም እንደ ሹመቱ ዋጋ አይሰጥም። “ወደዚህ ሰው እመለከታለሁ” ይላል፤ “ምስኪን መንፈሱም ወደ ተሰበረ በቃሌም ወደ ሚደነግጥ”። —The Signs of the Times, October 21, 1897.
ሐሙስ
፣ ሚያዚያ 09
5. የሰው ፍርድ ከመለኮታዊ ፍርድ ጋር ሲነጻጸር
ሀ. ቅዱሳት መጻሕፍት በዚህ ዓለም ውስጥ ብዙውን ጊዜ በጥንት ዘመን የታየው፣ በተለይ ደግሞ በዚህ ዘመን ያለውን የኅብረተሰብ አእምሯዊ ሁኔታ የሚገልጹት እንዴት ነው? ኢሳይያስ 59:14፣ 15
“የክፉ ወኪሎች ኃይላቸውን በማጣመርና በማጠናከር ላይ ናቸው። ለመጨረሻው ታላቅ ተጋድሎ እየተጠናከሩ ነው። በዓለማችን ውስጥ ታላቅ ለውጦች በቅርቡ ይከሰታሉ፣ እናም የመጨረሻዎቹ እንቅስቃሴዎች ፈጣን ይሆናሉ፡፡ . . .
“ጠላት ፍትህን በማጣመም እና የሰዎችን ልብ በራስ ወዳድነት ፍላጎት በመሙላት ተሳክቶለታል። . . . የተራቡ የሰው ልጆች ጩኸት ወደ አምላክ ፊት ዘውትር እየወጣ ነው፤ በጭቆናና ዝርፊያ ሰዎች ብዙ ሀብት እያከማቹ ነው።”—Testimonies for the Church, vol. 9, pp. 11, 12.
ለ. በሁከት ውስጥ ቢንሆንም እንኳን፣ በእግዚአብሔር መንገድ ለምን እንታመናለን? ኢሳይያስ 55:8፣ 9
“ውስን የሆነው የሰዎች አዕምሮ ወደ ዘላለማዊው እግዚአብሔር ምክር ለመግባት ወይም የአላማውን ውጤት ሙሉ በሙሉ መረዳት ባይችልም፣ የሰማይን መልእክቶች እጅግ በደበዘዘ ሁኔታ የሚረዱት ግን በራሳቸው ስህተት ወይም ግድየለሽነት ምክንያት ነው። በፍጡር አመለካከቶች፣ በሰዎች ባህልና የሃሰት ትምህርቶች ምክንያት፣ እግዚአብሔር በቃሉ የገለጣቸውን ታላላቅ ነገሮች ሰዎች በከፊል ብቻ እንዲረዱት የሚያደርጋቸው፣ የእግዚአብሔርን ባርያዎች ጨምሮ፣ የሰዎች አእምሮ የሚታወርበት አጋጣሚ አልፎ አልፎ ነው የሚባል አይደለም።—The Great Controversy, pp. 344, 345.
“እግዚአብሔር ለልጆቹ ያለው ሃሳብ እጅግ ምጡቅ የተባለ የሰው ሃሳብ ሊደርስበት ከሚችለው ሁሉ በላይ ነው። በቅዱስ ሕጉ የባሕርይውን ቅጂ ሰጥቶናልና።”—Testimonies for the Church, vol. 8, p. 63.
አርብ
፣ ሚያዚያ 10
የግል ግምገማ ጥያቄዎች
1. የሱስ ያደገበትን ቤት ከባቢ ሁኔታ ግለጽ።
2. የክርስቶስ ወንድሞች ያሳዩት ዝንባሌ በዛሬው ጊዜ የሚደገመው እንዴት ነው?
3. ስለ የሱስ ምን ተቃራኒ አስተያየቶች ተሰራጭተዋል?
4. የአይሁድ መሪዎች ለየሱስ ያሳዩትን መንፈስ ግለጽ።
5. በሰው እና በእግዚአብሔር መንገድ መካከል ያለውን ትልቅ ልዩነት ግለጽ።