Back to top

Sabbath Bible Lessons

ወንጌል እንደ ዮሐንስ መሠረት (ፍል ሁለት)

 <<    >> 
7ኛ ትምህርት ሰንበት፣ ግንቦት 09፣ 2017

ብርሃኑ ችላ ተባለ ወይስ ተንጸባርቀ?

የመታሰቢያ ጥቅስ፡- “እግዚአብሔር ብርሃኔና መድኃኒቴ ነው፤ የሚያስፈራኝ ማን ነው? (መዝሙረ ዳዊት 27:1)

ክርስቶስ «ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደዓለም ይመጣል፡፡» ዮሐ 1፡9 እያንዳንዱ ሰብዓዊ ፍጡር በክርስቶስ የሱስ ሕይወት እንደሚያገኝ ሁሉ እያንዳንዷ ነፍስም በእርሱ አማካይነት ከመለኮት ኃይል ከሚወጣው ብርሃን ጨረር ታገኛለች።”—Education, p. 29.

ለንባብ የተመረጠዉ መጽሐፍ፡   Testimonies for the Church, vol. 7, pp. 18–28. 

እሁድ ፣ ግንቦት 03

1. የተተነበየው ብርሃን

ሀ. መንፈስ ቅዱስ በኢሳይያስ በኩል ስለየሱስ የተናገረው እንዴት ነው? ኢሳ 49፡6

ለ. የሱስን ለአምላክ ለመወሰን ወደ ቤተ መቅደሱ በቀረበ ጊዜ ስምዖን የገለጸው እንዴት ነው? ይህስ ስለ ምን ነገር እንድናስብበት ይገፋፋናል? ሉቃስ 2፡32።

“አረጋዊዩ ስምዖን የሱስ ይህን ትምህርት በሰጠበት ቤተ መቅደስ ውስጥ ሆኖ ስለ የሱስ «እርሱ ለአረማውያን እውነትን የሚገልጥ ብርሃን ይሆናል፤ ለሕዝብህም ለእሥራኤል ክብር ነው» በማለት ተናግሮ ነበር። ሉቃ.2:32። ይህን በተናገረ ጊዜ ስምዖን እሥራኤላውያን የሚያውቁትን ትንቢት ስለ የሱስ መጥቀሱ ነበር። መንፈስ ቅዱስ በነቢዩ በኢሳይያስ አማካይነት “ለአንተ ለአገልጋዬ ያዘጋጀሁልህ ታላቅ ሥራ አለ፣ ይኸውም ከጥፋት ለተረፉት የእሥራኤል ሕዝብ እንደገና የታላቅነትን ክብር መስጠት ብቻ አይደለም፣ ነገር ግን ዓለም በመላው ይድን ዘንድ ለአሕዛብ ሁሉ ብርሃን አድርጌሃለሁ» በማለት ተናግሮ ነበር። ኢሳ.49:6። ይህ ትንቢት የተነገረው ስለ መሲሑ መሆኑ ይታወቅ ስለነበር የሱስ «እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ» ባለ ጊዜ እርሱ ይጠበቅ የነበረው መሲሕ መሆኑን እንደተናገረ ሕዝቡ በትክክል ገብቷቸዋል።”—The Desire of Ages, p. 465.

“ኦ! ይህ የቤተልሔም አስደናቂ ታሪክ ምን አይነት ትምህርት ነው! አለማመናችን፣ ኩራታችንና አንዳች-አይጎድለኝም ባይነታችንን እንዴት አድርጎ ይወቅሳል! በሚያስከስሰው ቸልተኝነታችን፣ የዘመኑን ምልክቶች ማወቅ ተስኖን የመጎብኘታችን ቀን ሳናውቀው እንዳንቀር፣ ጥንቁቅ እንድንሆን እንዴት አድርጎ እጅግ ያሳስበናል!”—The Great Controversy, p. 315.


ሰኞ ፣ ግንቦት 04

2. ችላ የተባለዉ (የተገፋዉ) ብርሃን

ሀ. የአይሁድ መሪዎች ለክርስቶስ ተልእኮ ምን ምላሽ ሰጡ? ዮሐንስ 1:11፤ 8፡13።

“መላው የክርስቶስ ህይወት እና ትምህርቶቹ ቀጣይነት ያለው የትህትና፣ የጎነት፣ የመልካምነት እና ራስን የመካድ ትምህርቶች ነበሩ። ይህ በራስ ጽድቅ ለሚያምኑ ለአይሁዶች የማያቋርጥ ተግሣጽ ነበር። ከነሱ ይልቅ የሕዝቡን ቀልብ እየሳቡ ስላሉ ስለ ክርስቶስ ድንቅ ሥራ በቅናት ሲናገሩ ያበዱ እስኪመስሉ ድረስ ሰይጣን መርቷቸዋል። እሱ አስመሳይ ነው ብለው ራሳቸው እንዲያምኑ እንዲሁም እሱን ለማጥፋት የሚጥሩበት ማንኛውም መንገድ ቢሆን መልካም እንደሆነ እንዲያምኑ አድርጓቸዋል።”—Spiritual Gifts, vol. 4a, p. 117.

ለ. የሱስ ለማያምኑት ፈሪሳውያን ምን ግልጽ ማብራሪያ ሰጥቷቸዋል—ነገር ግን እነሱ ምን ምላሽ ሰጡ? ዮሐንስ 8፡14-18

“[ፈሪሳውያን] የክርስቶስን መለኮታዊ ባሕርይና ተልእኮ አላውቁም ነበር፣ ምክንያቱም መመርመር መብትና ግዴታቸው የሆነዉን መሲሑን በሚመለከት የተነገሩትን ትንቢቶች እነሱ ግን አልመረመሩም ነበር። ከእግዚአብሔር እና ከሰማይ ጋር ምንም ግንኙነት አልነበራቸውም፣ ስለዚህም የአለምን አዳኝ ስራ አልተረዱም፣ በዚህም ምንም እንኳን የሱስ አዳኝ መሆኑን በጣም አሳማኝ ማስረጃ ቢሰጣቸውም፣ ለመረዳት አእምሮአቸውን ለመክፈት አልፈለጉም፡፡ በመጀመሪያ ልባቸውን እርሱን በመቃወም አጠነከሩ፣ እናም የእርሱን አምላክነት የሚያረጋግጡበትን ጠንካራ ማስረጃ ለማመን ፍቃደኛ አልነበሩም፣ እናም በዚህ ምክንያት፣ እርሱን ላለማመን እና ላለመቀበል እስኪወስኑ ድረስ ልባቸው እየደነደነ ሄደ።”—The Spirit of Prophecy, vol. 2, pp. 354, 355.

ሐ. የሱስ በራሱ እና በማያምነው ፈሪሳዊያን መካከል ምን ልዩነት እንዳለ ተናግሯል? ዮሐንስ 8፡19-23

መ. የአይሁድ ገዥዎች ክርስቶስን አለመቀበል የሚያስከትለው ገዳይ የሆነ ውጤት ምን ነበር? ዮሐንስ 8:24ማቴዎስ 23፡38


ማክሰኞ ፣ ግንቦት 05

3. ሁለቱ የአድማጭ ክፍሎች

ሀ. ፈሪሳውያን በኃጢአታቸው ሊሞቱ እንደሚችሉ ማስጠንቀቂያ ከተሰጣቸው በኋላ የሱስን ምን አሉት? ለምንስ? ዮሐንስ 8፡25 (የመጀመሪያ ክፍል)።

“የተናገረውን ከቁም ነገር ያልቆጠሩ በመምሰል «አንተ ማነህ?» ብለው ጠየቁት። ይህን ያሉበት ምክንያት ክርስቶስ ነኝ እንዲል ለማድረግ ነበር። የየሱስ ሁኔታና ሥራ ሕዝቡ ይጠብቀው ከነበረው የተለየ ስለ ነበር እነዚህ መሰሪ ጠላቶቹ በቀጥታ መሲሕ መሆኑን ቢናገር ሕዝቡ እንደ አታላይ ቆጥረው ችላ ይሉታል የሚል ግምት ነበራቸው።”—The Desire of Ages, p. 465.

ለ. ከአብ ጋር ያለውን ልዩ ግንኙነት በመግለጥ አዳኛችን እንዴት መለሰላቸው? ዮሐንስ 8፡25 (የመጨረሻው ክፍል)፣ 26–29

“ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ሕግ መሠረታዊ ሥርዓቶች ታማኝ ከመሆን ፈቀቅ አላለም። የአባቱን ፈቃድ የሚጻረር ነገር አላደረገም። በመላእክት፣ በሰዎች እና በአጋንንት ፊት እርሱን ደስ የሚያሰኘውን ሁል ጊዜ አደርጋለሁ በማለት ከማንኛውም ከሰዉ ዘር ከንፈር ቢወጣ ስድብ ቃል ሊሆን የሚችለውን ቃል እርሱ ግን ሊናገር ይችላል። ዮሐንስ ወንጌል 8፡29፡፡ ቀን በቀን ለሦስት ዓመታት ጠላቶቹ ተከታተሉት፣ በባህሪው ውስጥ ትንሽ እድፍ እንኳን ለማግኘት ይሞከሩ ነበር፡፡ ሰይጣን፣ ከክፉ ተባባሪው ጋር፣ ሊያሸንፈው ፈለገ። ነገር ግን የሚያሸንፉበትን ምንም አላገኙበትም። ሰይጣናት እንኳ፡ ‘አንተ የእግዚአብሔር ቅዱስ ነህ’ ብለው እንዲናዘዙ ተገድደዋል።”—Testimonies for the Church, vol. 8, p. 208.

ሐ. የክርስቶስን ከአባቱ ጋር ያደረገውን የዕለት ተዕለት ጉዞ እና ያንን ተሞክሮ እንዴት ማንጸባረቅ እንዳለብን ግለጽ። ዮሐንስ 15:10ኤፌሶን 2፡4-6

“የሱስ በሰው ተፈጥሮ ሆኖ እንደተመላለሰ እንዲሁ የእግዚአብሔርም ተከታዮቹ እንዲሆኑ ነው። በእሱ ጥንካሬ አዳኝ የኖረበትን የንጽህና እና የቅድስና ህይወት መኖር አለብን።”—Ibid., p. 289.

“የአዳኙ በምድር ላይ የኖረበት ህይወት፣ ምንም እንኳን በተጋድሎ መካከል ቢኖርም፣ የሰላም ህይወት ነበር። የተቆጡ ጠላቶች ዘወትር ያሳድዱት ሳሉ እሱ ግን፡- “የላከኝ ከእኔ ጋር ነው፤ አብ ብቻዬን አልተወኝም፤ ሁልጊዜ እርሱን ደስ የሚያሰኘውን አደርጋለሁና” አለ። ዮሐንስ ወንጌል 8፡29 የትኛውም የሰው ወይም የሰይጣን ቁጣ ከአምላክ ጋር ያለውን ፍጹም ኅብረትና መረጋጋት ሊረብሽ አይችልም።”—Thoughts From the Mount of Blessing, pp. 15, 16.


ረቡዕ ፣ ግንቦት 06

4. ብርሃኑ ለሌሎች ተንጸባርቋል

ሀ. ክርስቶስ ለፈሪሳውያን ጠቃሚ የሆኑ እውነቶችን በተናገረበት ወቅት የተናገራቸው ቃላት ቅን አድማጮችን ልብ የነካው እንዴት ነው? ይህስ ዛሬ እኛን ሊያበረታታን የምችለው ለምንድን ነው? ዮሐንስ ወንጌል 8፡30

“ክርስቶስ በተረጋጋ፣ አስተዋይ በሆነ መንገድ እንዴት መሥራት እንዳለበት እና እሱን ወደ ኩነኔ ለማምጣት የሚያወጡትን እቅዳቸውን እንዴት ከንቱ እንደሚያደርግ ተረድቷል። የጌታ ቃላቶች ወደ እላማው እንደሚነደፉ እንደተሳሉ ፍላጻዎች ነበሩና፣ የከሳሾቹን ልብ ያቆስሉ ነበር። ክርስቶስ ሰዎችን ባነጋገረ ቁጥር፣ ሰሚዎቹ በዕድሜ ትልቅም ይሁኑ ትንሽ፣ ቃላቱ በአንዳንድ አድማጮቹ ነፍስ ላይ የማዳን እርምጃን ይወሰዱ ነበር። ከክርስቶስ አንደበት የወጣ ማንኛዉም መልእክት በከንቱ አልጠፋም። የተናገራቸው ቃላት ሁሉ በሰሙት ላይ አዲስ ሃላፊነትን ይጥሉ ነበር። የመጨረሻውን የምሕረት መልእክት ለዓለም የሚያደርሱ፣ እውነትን በቅንነት የሚያቀርቡ፣ በእግዚአብሔር ኃይል የሚታመኑ አገልጋዮች፣ ጥረታቸው ከንቱ ይሆናል ብለዉ በፍጹም መፍራት የለባቸውም። የእውነት ፍላጻ ወደ እላማው አልሄደም፣ የሰሚውንም ነፍስ አልወጋም ሊል የሚችል ማንም የለምና። ምንም እንኳን የእውነትን ፍላጻ አካሄድ የሰው ዓይን ሊያየው ባይችልም፣ የቆሰለውንም ነፍስ ጩኸት የሰዉ ጆሮ ባይሰማም፣ እውነት ግን በጸጥታ ወደ ልብ መንገዷን ትገሰግሳለች። እግዚአብሔር ለነፍስ ተናግሯል፣ እናም በመጨረሻው የፍርድ ቀን የእግዚአብሔር አገልጋይ ክብር ለሚገባው ለክርስቶስ ክብርን ለመስጠት ከማዳን የጸጋ ሽልማቶች ጋር ይቆማል። በስውር የሚያይ አምላክ፣ እውነትን በስሙ ለተናገሩት በግልጥ ይከፍላቸዋል።”—The Signs of the Times, February 6, 1896.

ለ. ከአገልጋዮች በተጨማሪ የሰማይን ብርሃን በማንፀባረቅ የሚባረከ ማን አለ? መዝሙር 27:1፤ 147:15፤ ኢሳይያስ 55:10፣ 11

“ለአገልግሎት ያልተጠሩ ሰዎች እንደ ችሎታቸው መጠን ለመምህሩ እንዲሠሩ መበረታታት አለባቸው። በአሁኑ ጊዜ ያለ ምንም ሥራ የተቀመጡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወንዶች እና ሴቶች ለአምላክ አስፈላጊ አገልግሎት ሊሰጡ ይችላሉ። እውነትን ወደ ጓደኞቻቸው እና ጎረቤቶቻቸው ቤት በማድረስ፣ ለመምህሩ ታላቅ ስራ ሊሰሩ ይችላሉ። እግዚአብሔር ለሰው ፊት አያዳላም። ልክ እንደሌሎች ጥልቅ የሆነ ትምህርት ባይማሩም እንኳ እሱ ራሳቸውን የሰጡ ትሑት ክርስቲያኖችን ይጠቀማል። እንደነዚህ ያሉት ሰዎች ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ እሱን እንዲያገለግሉ ይደረጉ። ትሑት፣ ልባም እና አምላካዊ ባሕርይ የተላበሱ ከሆኑ—አንድ የተቀባ አገልጋይ ማድረግ ከሚችለው በላይ የቤተሰብን እውነተኛ ፍላጎት ለማሟላት ብዙ ማድረግ ይችላሉና።”—Testimonies for the Church, vol. 7, p. 21.


ሐሙስ ፣ ግንቦት 07

5. ባርነት ከነጻነት ጋር ሲነጻጸር

ሀ. የሱስ እሱን ለተቀበሉት አይሁዶች ምን ብሏቸዋል? ዮሐንስ 8:31፣ 32 በአንጻሩ ግን የማያምኑት ከኃጢአት ነፃ የሚያደርገንን ብቸኛውን ሁኔታ ማየት የተሳናቸው እንዴት ነው? ዮሐንስ ወንጌል 8፡33-36

“[ፈሪሳውያን] የክፉ መንፈስ ተገዥ ስለነበሩ ከሁለም በከፋ ባርነት ሥር ነበሩ።

“ራሱን ለእግዚአብሔር ለማስረከብ ፈቃደኛ የማይሆን ነፍስ በሌላ ኃይል ቁጥጥር ሥር ነው። የራሱ አዛዥ አይደለም። ስለ ነፃነት ይናገር ይሆናል፤ ነገር ግን በጣም አሰቃቂ በሆነ ባርነት ሥር ነው ያለው። አእምሮውን ሰይጣን ስለሚቆጣጠረው የእውነትን ውበት ለማየት አይፈቀድለትም። ምንም እንኳን የራሴን የሕሊና ፍርድ ነው የምከተለው በማለት ራሱን ቢደልልም የጨለማውን መስፍን ፍላጐት ነው የሚፈጽመው። የሱስ የመጣው የኃጢአት ባርነትን እግር ብረት ሰብሮ ነፍስን ነፃ ለማውጣት ነው። …

“በማዳን ሥራ ማስገደድ የሚባል ነገር የለም። በውጫዊ ኃይል መጠቀምም የለም። በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት እያንዳንዱ ሰው ማንን ለማገልገል እንደሚፈልግ ራሱ እንዲወሰን ይደረጋል። አንድ ሰው ራሱን ለክርስቶስ በማስረከቡ ምክንያት በሚከሰተው ለውጥ ከፍተኛ የሆነ የነፃነት ስሜት ይፈጠራል። ኃጢአትን የመተው ሥራ የግለሰቡ ጉዳይ ነው። እርግጥ ነው ራሳችንን ከሰይጣን ቁጥጥር ነፃ ለማድረግ አቅም የለንም፣ ነገር ግን ከኃጢአት አርነት ለመውጣት ፍላጐት ሲያድርብንና ከእኛ ውጭና በላይየሆነ ኃይል ለማግኘት ስንጮህ ነፍሳችን መለኮታዊ በሆነው በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ይሞላና የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለመፈጸም በፍላጐት ይንቀሳቀሳል።

“ሰው ነጻነቱን ለማግኘት የሚያስችለው ብቸኛው ውል ከክርስቶስ ጋርአንድነት መፍጠር ነው። “እውነትም ነጻ ያወጣችኋል!» እውነቱም ክርስቶስ ነው። ኃጢአት በሰው ላይ ድል የሚጐናጸፈው አእምሮን በማዳከምና የነፍስን ነጻነት በመደምሰስ ነው። ለእግዚአብሔር መገዛት ማለት ወደ እውነተኛው ሰብአዊ ደረጃ ማለትም ወደ እውነተኛው ማዕረግና ሰብአዊ ክብር ተመልሶ መምጣት ማለት ነው። እንድንተዳደርበት የተደነገገ ልን መለኮታዊ ሕግ የነጻነት ሕግ ነው። ያዕ.2:12።”—The Desire of Ages, p. 466.


አርብ ፣ ግንቦት 08

የግል ግምገማ ጥያቄዎች

1. ስምዖን ስለ የሱስ የተናገረውን ሐሳብ አስፈላጊነት ግለጽ።

2. ጸሐፍትና ፈሪሳውያን በክርስቶስ ላይ የነበራቸውን አስተሳሰብ ግለጽ።

3. አይሁዳዊያን የሱስን በመቃወማቸዉ ምን ይደርስባቸዋል?

4. በዚያን ጊዜም ሆነ አሁን ቅን የሆኑ ነፍሳት ለክርስቶስ ምን ምላሽ ይሰጣሉ?

5. የ“ነጻነት” ጽንሰ-ሐሳብን በወንጌል እውነት ብርሃን አብራራ።

 <<    >>