እሁድ
፣ ሚያዚያ 19
1. ለየሱስ የተዘጋጀ ወጥመድ
ሀ. የሱስ በቤተ መቅደሱ ውስጥ እያስተማረ ሳለ ጻፎችና ፈሪሳውያን ምን አደረጉ? ዮሐንስ 8፡2-3
“[ክርስቶስ]ብዙም ሳይቆይ ትምህርቱን ማቋረጥ ነበረበት። ፈሪሳውያንና ጸሐፍት በድንጋጤ ግራ የገባት ሴት እየጐተቱ ሰባተኛውን ሕግ ስለመሻርዋ ክሳቸውን በከፍተኛ ድምጽ እያሰሙ ወደ የሱስ መጡ።”—The De¬sire of Ages, p. 460.
ለ. ፈሪሳውያን ለህግ ከፍተኛ አክብሮት በማሳየታቸው ለክርስቶስ ምን ጥያቄ አቅርበው ነበር? ዓላማቸውስ ምን ነበር? ዮሐንስ 8፡4-6 (የመጀመሪያ ክፍል)።
“ለይምሰል ያህል ያሳዩት አክብሮት እርሱን ለማጥፋት የጠነሰሱት ሥርየሰደደ ሴራ ሽፋን ነበር። ምንም ዓይነት ውሳኔ ቢወስን እርሱን ለመክሰስ በቂ ምክንያት አናጣም በማለት ለውንጀላ እንዲያመቻቸው ሲሉ ይህን አጋጣሚ ተጠቀሙበት። ሴትዮዋን በነጻ ቢለቃት የሙሴን ሕግ ችላ ብሏል የሚል ክስ ይቀርብበታል፣ የሞት ፍርድ ቢወስንባትም የሮማውያንን ሥልጣን በመሻማት ይወነጀላል።”—Ibid., pp. 460, 461.
ሰኞ
፣ ሚያዚያ 20
2. እውነተኛው ምስል ተገለጠ
ሀ. የሱስ ለፈሪሳውያን ውሸት ምን ምላሽ ሰጠ? ዮሐንስ 8፡6 (የመጨረሻው ክፍል)።
“የሱስ ሁኔታውን አጤነ፣ ማለትም በሐፍረት የምትርበደበደውን ሴትና ሰብአዊ ርህራሄ የጐደለውን የመኳንንቱን የጭካኔ ገጽታ ተመለከተ። እንከን የሌለው ንጹሕ መንፈሱ በዚያ ትዕይንት ምክንያት ተሸማቀቀ። የሱስ ይህ ክስ ለምን ምክንያት ወደ እርሱ እንደመጣ ጠንቅቆ ያውቅ ነበር። ከዚያ የነበሩትን ሰዎች የእያንዳንዳቸውን ልብ በማንበብ ባሕርያቸውንና የሕይወት ታሪካቸውን ያውቅ ነበር። እነዚህ አቃቤ ሕግ መሆን የሚገባቸው ሰዎች የሱስን ለማጥመድ ሲሉ የእነርሱ ሰለባ የሆነችውን ሴት ኃጢኣት እንድ ትሠራ ያደረግዋት ራሳቸው ናቸው። የሱስም የከሳሾቹን ጥያቄ ያዳመጠ ባለመምሰል ጐንበስ ብሎ ወደ መሬት እየተመለከተ በአፈሩ ላይ መጻፍ ጀመረ።”—The Desire of Ages, p. 461.
ለ. የሱስ ከሳሾቹ ራሳቸው ኃጢአት አልባ እንዳልሆኑ ያሳየው እንዴት ነው? እነሱስ ምን አደረጉ? ዮሐንስ 8፡7-9
“ከሳሾቹ ተረቱ። አሁን የይስሙላ ቅድስና ካባቸው ተቀድዶ ዘላለማዊ ንጽሕና ባለው ጌታ ፊት ኃጢአተኛና ወንጀለኛ ሆነው ቆሙ። ስውር ኃጢአ ታቸው ለሕዝቡ ይገለጽብናል ብለው በመፍራት እየተርበደበዱ የእነርሱ ሰለባ የሆነችውን ሴት ከርህሩሁ ጌታ ጋር ትተው አንገታቸውን አቀርቅረው አንድ በአንድ ሾልከው ጠፉ።”—Ibid
ሐ. በአጠቃላይ፣ የሱስ ለከሳሾቹ ከተናገራቸው ቃላት ምን እንማራለን? ሉቃስ 6፡42
“ለእነርሱ ስህተት መስሎ የሚታያቸውን ነገሮች ለማሻሻል ብስለት የጎደለው ፍላጎት ያላቸው ሰዎች አሉ። ስህተት የሰራውን ሰው ለመተካት እኛ ራሳችን መመረጥ አለብን ብለው ያስባሉ። ሌሎች ዳር ቆመው እያዩ እና እየተቹ እነዚህ ሰራተኞች የሰሩትን ሥራ ዋጋ ዝቅ አድርገው ይመለከቱታል። በተግባራቸው እንዲህ ይላሉ፡- ‘እኛ ታላቅ ነገሮችን ማድረግ እንችላለን። ሥራውን በተሳካ ሁኔታ ማከናወን እንችላለን።' ለእንደነዚህ ላሉ ስህተትን እንዴት እንደሚያስወግዱ ጠንቅቀው የሚያውቁ ለሚመስላቸው፡- ‘እንዳይፈረድባችሁ አትፍረዱ’ እንድል ታዝዣለሁ። ማቴዎስ 7፡1፡፡ እነዚህ ወንድሞች በአንዳንድ ነጥቦች ላይ ስህተቶችን ሊያስወግዱ ይችላሉ፣ ነገር ግን በሌሎች ነገሮች ላይ ለማስተካከል በጣም ከባድ እና በስራው ውስጥ ግራ መጋባትን የሚያመጣ ከባድ ስህተቶችን የመስራት ትልቅ አጋጣሚ ያላቸው ናቸው፡፡ እነዚህ ስህተቶች ወንድሞቻችሁ ከሰሩት የበለጠ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ ናቸው።”—Testimonies for the Church, vol. 7, p. 279.
ማክሰኞ
፣ ሚያዚያ 21
3. ያልተጠበቀ ድርጊት
ሀ. የሱስ ከሳሾቿ ከሄዱ በኋላ ሴቲቱን ምን ጥያቄ ጠየቃት? ሁኔታውን የያዘበት መንገድስ ሕይወቷን የሚነካው እንዴት ነው? ዮሐንስ 8:10፣ 11
“ሴቲቱም በፍርሃት ተሸማቅቃ በየሱስ ፊት ቆመች። ‘ከእናንተ ኃጢአት የሌለበት አስቀድሞ በድንጋይ ይውገራት’ የሚለው የየሱስ ቃል የሞት ፍርድ ብያኔ ሆኖ ነው የተሰማት። ቀና ብላ የአዳኙን ፊት ለማየት አልደፈረችም ፣ ነገር ግን በዝምታ ሞቷን እየጠበቀች ነበር። ከሳሾቿ ዝም ብለው ሲሄዱ አየቻቸውና በመገረም ግራ ተጋብታ ነበር፤ “እኔም አልፈርድብሽም፤ ሂጂና ደግመሽ ኃጢአት አትሥሪ” የሚል የተስፋ ቃል በጆሯ ተሰማ። ልቧ ቀለጠ፣ በየሱስ እግር ስር ወድቃ፣ ከምስጋናና ፍቅር ብዛት እየተንሰቀሰቀችና እንባዋን እያፈሰሰች ኃጢአቷን ተናዘዘች።
“ያቺ ወቅት ለእርሷ የንጽህና፣ የሰላምና በእግዚአብሔር አገልግሎት የተቀደሰ የአዲስ ሕይወት ጅማሬ ነበረች። የሱስ የዘላለም ሞት የሚያስከትለውን የዚህችን ሴት መንፈሳዊ ደዌ በመፈወሱ አጅግ በጣም አስከፊ የሆነን ሥጋዊ በሽታ ሁሉ ከመፈወስ የበለጠውን ታላቁን ተዓምራት አከናወነ። ይህቺ የንስሓ የገባች ሴት ከፅኑ ተከታዮቹ አንዷ ሆነች። ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ ፍቅር እና ታማኝነት ለይቅርታው ምህረቱ ምስጋናዋን አሳይታለች። አለም ለዚች ለተሳሳተች ሴት ነበረው ንቀትና ጥላቻ ብቻ ነበር፤ ኃጢአት የሌለበቱ ግን ስለድካሟ አዘነ፣ የእርዳታ እጁን ዘረጋላት። ግብዞች ፈሪሳውያን ሲያወግዙት የሱስ “እኔም አልፈርድብሽም፤ ሂጂና ደግመሽ ኃጢአት አትሥሪ” አላት።”—The Ministry of Healing, p. 89.
“ይህቺን ሴት ይቅር በማለቱና የተሻለ ሕይወት እንድትኖር በማደፋፈሩ የየሱስ ባሕርይ ፍጹም የሆነ የቅድስና ውበት ያንጸባርቃል። የሱስ ኃጢአትንና ኃጢአተኛነትን አድበስብሶ ማለፍ ባያውቅም ማዳን እንጂ መኮነን አይሻም። ይህቺ የተሳሳተች ሴት ከዓለም ያገኘችው ንቀትንና ጥላቻን ሲሆን የሱስ ግን የማጽናኛና የተስፋ ቃላት ተናገራት።”—The Desire of Ages, p. 462.
ለ. የክርስቶስን የማዳን ጸጋ ውጤት ግለጽ። ሉቃስ 7:37–40፣ 47፣ 48
“የሱስ የእያንዳንዱን ነፍስ ሁኔታ ያውቃል። የኃጢአተኛው ጥፋተኝነት እንደበዛ መጠን አዳኙ አብልጦ ያስፈልገዋል። የእርሱ የመለኮት ፍቅር እና የርህራሄ ልቡ ከሁሉም ይልቅ በጠላት ወጥመዶች ውስጥ ተስፋ የለሽ ሆኖ ለተጠላለፈው ሰው የተዘጋጀ ነው። በገዛ ደሙ የሰው ዘር ነጻ መውጣቱን የሚያመላክተውን ሰነድ ፈረመ።”—The Ministry of Healing, pp. 89, 90.
ረቡዕ
፣ ሚያዚያ 22
4. አጽናኞች በውጭ ሀገራት ተሰራጩ
ሀ. በተለይ ከሌሎች ጋር በተያያዘ አመለካከታችንን ሊሆን የሚገባው ምንድን ነው - እና ይህስ እንዴት ብቻ ሊሆን ይችላል? 2ኛ ቆሮንቶስ 1፡3-5
“ሁኔታዎችን ከነፍስ ልምምዶች ጋር የሚያገናኘው ጥቂት ነገር ነው። ለድርጊታችን ሁሉ መልክ የሚሰጠው በእኛ ዘንድ የሚወደደው መንፈስ ነው። ከእግዚአብሔር እና ከባልንጀሮቹ ጋር ሰላም ያለው ሰው አሳዛኝ ሰው ሊሆን አይችልም። ምቀኝነት በልቡ ውስጥ አይኖርም፤ ክፉ ሐሜት በእሱ ቦታ አያገኝም፤ ጥላቻ ከእሱ ዘንድ ሊኖር አይችልም፡፡ ከአምላክ ጋር የሚስማማ ልብ በዚህ ሕይወት ከሚያስጨንቁ ሁኔታዎችና ፈተናዎች በላይ ከፍ ከፍ ይላልና።”—Testimonies for the Church, vol. 5, p. 488.
“የሱስ የማጽናናት አገልግሎት ያገኘው በመከራ ነው። በሰው ልጅ መከራ ሁሉ እርሱ ተጨንቋል፤ እርሱ ራሱ ተፈትኖ መከራን ስለ ተቀበለ የሚፈተኑትን ሊረዳቸው ይችላል። ኢሳይያስ 63:9፤ ዕብራውያን 2፡18 ከክርስቶስ ጋር መከራ የመካፈልን ኅብረት የተቀላቀለ ነፍስ ሁሉ በዚህ አገልግሎት የመካፈል መብት አለው።”—Thoughts From the Mount of Blessing, p. 13.
ለ. የክርስቶስን ፈለግ በመከተል የምናገኘውን ልዩ ተስፋ እና እድል ግለጽ። 2ኛ ቆሮንቶስ 1:6፣ 7
“የክርስቶስ መከራ ተካፋይ መሆን ክብር እንደሆነ ካልተሰማችሁ፤ ለጥፋት ለተዘጋጁት የነፍስ ሸክም ካልተሰማችሁ፤ ሊሠራ የሚገባው ሥራ እንዲሠራ ገንዘብንና ንብረትን ለመሠዋት ፍቃደኛ ካልሆናችሁ፥ በእግዚአብሔር መንግሥት ለእናንተ ቦታ አይኖራችሁም። በእያንዳንዱ እርምጃ ከክርስቶስ ጋር የመከራው እና ራስን የመካድ ተካፋይ መሆን አለብን።”—Testi¬monies for the Church, vol. 9, pp. 103, 104.
ሐ. በሦስቱ መላእክት መልእክት ውስጥ በአማኞች መካከል በጣም የሚፈለጉ ባሕርያት ግለጽ። 1ኛ ቆሮንቶስ 13:13፣ 4–8
“የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት ጠባቂ ሕዝቦች ልንከባከቧቸው የሚገቡ በጣም አስፈላጊዎቹ ባሕርያት ትዕግሥትና መቻል፣ ሰላምና ፍቅር ናቸው። ፍቅር ሲጎድል ወደ ሊካካስ የማይችል ኪሳራ ይኖራል።”—Ibid., vol. 6, p. 398.
ሐሙስ
ሚያዚያ 23
5. በየዋህነት ፍቅር መመለስ
ሀ. ሐሰተኛ ልብ ያላቸው አማኞች ብዙ ጊዜ ከሚያደርጉት በተቃራኒ አንድ ክርስቲያን በኃጢአት ቢወድቅ እውነተኛ አማኞች እሱን ለመመለስ እንዴት ይሠራሉ? ገላትያ 6:1-3፤ ሮሜ 15፡1-3
“ኃጢዘተኛውን የመመለስ ስራ የኛ ሸክም መሆኑን አስታውስ። ይህ ሥራ በትዕቢት፣ በሥልጣን፣ በጌትነት የሚሠራ አይደለም። በእራስህ መንገድ፣ ‘ሥልጣን አለኝና እጠቀምበታለሁ’ አትበል፣ እናም በተሳሳተ ሰው ላይ ውንጀላ (ክስ) አትድፋ። አንተ ደግሞ እንዳትፈተን ራስህን እየጠበቅህ፣ ኃጢአተኛውን የመመለስን ሥራ 'በየዋህነት መንፈስ አድርግ። ለወንድሞቻችንን እንድንሠራ ከፊታችን የተቀመጠው ሥራ እነርሱን ወደ ጎን እንድንጥላቸው አይደለም፣ ‘አበሳጭተህኛልና እኔም ልረዳህ አልፈልግም’ በማለት ተስፋ እንዲቆርጡ ወይም እንዲጠፉ ማድረግ አይደለም። ራሱን በጥበብና በብርታት የተሞላ ሰውአድርጎ የሚያሳብ፣ የተጨቆነውንና የተጨነቀውን፣ እርዳታን የሚሻውን የማይረዳ፣ የፈሪሳዊውን መንፈስ የሚገልጥና ራሱን በራሱ ባዘጋጀው የክብር ልብስ የሚያጀቡን ሰው ነው። እርሱ በመንፈሱ እንደ ሌሎች ሰዎች ባለመሆኑ፣ አካሄዱ የተመሰገነ እንዲሁም ቢፈተን እንኳን የማይወድቅ በጣም ጠንካራ እንደሆነ አድርጎ በማሰቡ እግዚአብሔርን ያመሰግናል፡፡ ነገር ግን 'አንድ ሰው ምንም ሳይሆን ምንም የሆነ ቢመስለው ራሱን ያታልላልና።' ቁጥር 3”—Testimonies for the Church, vol. 6, pp. 398, 399.
“ስህተት የሚሠሩን ሰዎች ለማሳጣት ግንባርቀደም በመሆን እነዚህን ሰዎች ለመክሰስ ጉጉት ያለባቸው ሁሉ አብዛኛውን ጊዜ በሕይወታቸው አንድ እንከን ያለባቸው ናቸው። ሰዎች ኃጢኣትን እየወደዱ ኃጢአተኞችን ይጠላሉ። ክርስቶስ ኃጢኦትን ይጠላል፣ ኃጢአተኞችን ግን ይወዳል። የክርስቶስ ተከታዮች የሆኑ ሁሉ ይህ ዓይነት መንፈስ ሊኖራቸው ይገባል። ክርስቲያናዊ ፍቅር ለመገሰጽ የማይቸኩል፣ ንስሐ የመግባትን ምልክት ፈጥኖ የሚረዳ፣ ይቅር ለማለት፣ ለማበረታታት፣ የተሳሳተን ሰው ወደ ቅድስና ለመመለስና ከቅድስና መንገድ እንዳይወጣ ለማድረግ ዝግጁ ነው።”—The Desire of Ages, p. 462.
አርብ
ሚያዚያ 24
የግል ግምገማ ጥያቄዎች
1. ጸሐፍትና ፈሪሳውያን ለየሱስ ያዘጋጁትን ወጥመድ ግለጽ።
2. ግብዞች አይሁዳውያን ለህግ አክብሮት ያሳዩት እንዴት ነው?
3. ከሳሾቹ አይሁዶች ስለ ራሳቸው ምን እንዲያምኑ ተገደዱ?
4. በደል የደረሰባት ሴት ያገኘችሁን ተስፋ ግለጽ።
5. ከተሳሳቱ ነፍሳት ጋር በምገናኝበት ጊዜ የሱስን መምሰል የምችለው እንዴት ነው?