Back to top

Sabbath Bible Lessons

ወንጌል እንደ ዮሐንስ መሠረት (ፍል ሁለት)

 <<    >> 
13ኛ ትምህርት ሰንበት፣ ሰኔ 21፣ 2017

ትንሳኤ እና ህይወት

የመታሰቢያ ጥቅስ፡- “የሱስም። ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል። (ዮሐንስ 11፡25)።

“ለሚያምን ሰዉ ሞት ከባድ ነገር አይደለም። ክርስቶስ ሞት የአጭር ጊዜ ጉዳይ መሆኑን ይናገራል። . . . ለክርስቲያን ሞት የእንቅልፍ፣ በጨለማ ዝምታ የሰፈነበት ጥቅት ጊዜ ነው። ሕይወቱ ከክርስቶስ ጋር በእግዚአብሔር ተሰውሮአልና።”—The Desire of Ages, p. 787.

ለንባብ የተመረጠዉ መጽሐፍ፡   Selected Messages, bk. 1, pp. 296–300. 

እሁድ ፣ ሰኔ 15

1. የሱስ በቢታንያ

ሀ. ማርታ የሱስ ወደ ቢታንያ እንደሚመጣ ስትሰማ ምን አደረገች? ምን እምነት ነበራት? ዮሐንስ 11፡20-22

“ከሐዘንተኞቹ መካከል አንዳንዶቹ በኢየሩሳሌም ከፍተኛ ሥልጣን የነበራቸውና ከሟቹ ቤተሰብ ጋር ዝምድና የነበራቸው ነበሩ። ከነዚህ መካከል አንዳንዶቹ ክርስቶስን አምርረው የሚጠሉ ነበሩ። ክርስቶስ ሐሳባቸውን ስለሚያውቅ ወዲያውኑ ማንነቱን አላሳወቀም።

“በክፍሉ ውስጥ አብረዋት የነበሩት ሰዎች ሳይሰሙ የየሱስ መምጣት በምስጢር ለማርታ ተነገራት። …

“ማርታ ልብዋ በሚጋጩ ስሜቶች እየታወከ ጌታን ለመገናኘት ገሰገሰች። ስሜቱ ጐልቶ በሚታይበት በጌታ ፊት ላይ ምንጊዜም የማይጠፋው የርህራሄና የፍቅር ስሜቱ ታያት። በእርሱ የነበራት እምነት የማይናወጥ ቢሆንም የሱስ ያፈቅረው ስለነበረው ውድ ወንድምዋ ታስብ ነበር። ክርስቶስ ቀደም ብሎ ባለመምጣቱ የሐዘን ስሜት እየተናነቃት አሁንም ቢሆን እነርሱን ለማጽናናት አንድ ነገር ማድረግ እንደሚችል ተስፋ በማድረግ «ጌታ ሆይ! አንተ እዚህ ብትሆን ኖሮ ወንድሜ ባልሞተም ነበር» አለችው። በሐዘንተኞቹ ሁካታ መካከል እህትማማቾቹ እነዚህን ቃላት በመደጋገም ይናገሩ ነበር።

“የሱስ በመለኮታዊና በሰብአዊ ርህራሄ ስሜት በሐዘንና በጭንቀት የዛለውን የማርታን ፊት ተመለከተ። ማርታ ያለፈውን ሁኔታ የመዘርዘርዝንባሌ ሳይኖራት ሁሉንም ነገር «ጌታ ሆይ! አንተ እዚህ ብትሆን ኖሮ ወንድሜ ባልሞተም ነበር» በሚሉ የሐዘን ቃላት ገለጸችው። የፍቅርገጽታውን እየተመለከተች «አሁንም የምትለምነውን ሁሉ እግዚአብሔርእንደሚሰጥህ ዐውቃለሁ» አለች።—The Desire of Ages, pp. 529, 530.


ሰኞ ፣ ሰኔ 16

2. የመጨረሻው የተስፋ ቃል

ሀ. የሱስ ለማርታ ምን አረጋገጠላት? ዮሐንስ 11፡23 በዚህም ምን ተረዳች? ዮሐንስ 11፡24

“የሱስም “ወንድምሽ ከሞት ይነሣል» በማለት እምነትዋን አጠናከ ረላት። የክርስቶስ መልስ ቅጽበታዊ ለውጥ ተስፋ የማድረግ ስሜትን የሚቀሰቅስ አልነበረም። ይህ የየሱስ መልስ የማርታን አስተሳሰብ ከጊዜያዊዩ የወንድምዋ ከሞት መነሳት ባሻገር ወደ ጻድቃን ትንሣኤ እንዲያተኩርአደረገው። የሱስ ይህን ያደረገበት ምክንያት የአልዓዛር ከሞት መነሳት የሞቱ ጻድቃን ሁሉ ከሞት የሚነሱ ለመሆኑ ማረጋገጫ መሆኑንና ይህም የሚከናወነው በአዳኛችን ኃይል የመሆኑን እርግጠኛነት እንድትረዳ ለማድረግ ነበር።

“ማርታም «በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ ጊዜ ከሞት እንደሚነሳ

ለ. የሱስ ማርታ የነበራትን እምነት እውቅና የሰጠው በምን ቃል ነው? ዮሐንስ 11:25፤ 1ኛ ዮሐንስ 5፡12

“አሁንም እምነትዋን ትክክለኛ አቅጣጫ ለማስያዝ ሲል የሱስ «ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ» ሲል ገለጸላት። የክርስቶስ ሕይወትነት ከጥንት ከመሠረቱ ከራሱ የመነጨ እንጅ በብድር ወይም በውሰት ከሌላ የተገኘ አይደለም። «የእግዚአብሔር ልጅ ያለው ሕይወት አለው» 1ዮሐ.5:12። የክርስቶስ መለኮታዊነት ለምዕመናን የዘላለም ሕይወት ማግኛ ዋስትና ነው።”—Ibid.

ሐ. ከመቃብር ባሻገር ስላለን ተስፋ መሠረት የሆነው የትኛው ተስፋ ነው? የማርታ እምነት ከክርስቶስ ተአምር ጋር ምን ግንኙነት አለው? ዮሐንስ 5:26፤ 11:26፣ 27

“ከዚህ ላይየሱስ ዳግመኛ የሚመጣበትን ጊዜ ያስታውሳል። በዚያን ጊዜ የሞቱ ጻድቃን ይነሳሉ፣ በሕይወት ያሉ ጻድቃንም ሞትን ሳያዩ ወደ ሰማይ ይነጠቃሉ። ክርስቶስ አልዓዛርን ከሞት በማስነሳት የሠራው ተአምር የሞቱ ጻድቃንን ትንሣኤ ያመለከታል። የሱስ በቃሉም ሆነ በተግባሩ የትንሣኤ ሥልጣን ያለው መሆኑን ገለጸ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ በመስቀል ላይ የሚሞተው አምላክየሞትን ቁልፍ በመያዙና የመቃብር አሸናፊ በመሆኑ የዘላለም ሕይወት ለመስጠት ያለውን መብትና ኃይል አረጋገጠ።”—Ibid.


ማክሰኞ ፣ ሰኔ 17

3. የሱስ አለቀሰ

ሀ. በሐዘን የተደቆሰችውን የማርያምን ድርጊትና ቃል ግለጽ። ዮሐንስ 11፡28-32

ለ. የሱስ ማርያምና አንዳንድ አይሁዳውያን ሲያለቅሱ ሲመለከት ምን አደረገ? ለምንስ? ዮሐንስ 11፡33-35

“«የሱስ እርስዋ ስታለቅስና አብረዋት የመጡትም አይሁዳውያን ሲያለቅሱ ባየ ጊዜ በመንፈሱ አዝኖ ታወከ።» የሱስ ከዚያ የተሰበሰቡትን ሰዎች ልብ አነበበ። ከዚያ ከነበሩት ሰዎች መካከል ብዙዎቹ የገለጹት የሐዘን ስሜት ለማስመሰል እንጅ ከልባቸው አለመሆኑን ተመለከተ። ከሕዝቡ ጋርተቀላቅለው ልባዊ ያልሆነ የሐዘን ስሜት ይገልጹ የነበሩት ሰዎች ከጥቂት ጊዜ በኋላ ታላቅ ተአምር የሚሠራውን ሰው ብቻ ሳይሆን ከሞት የሚነሳውንም ጭምር ለመግደል እንደሚያስቡ ያውቅ ነበር። ክርስቶስ የግብዝነታቸውን ካባ ከላያቸው አንስቶ በመጣል ሊያጋልጣቸው ይችል ነበር። ነገር ግን የጽድቅ ቁጣውን ከመግለጽ ተቆጠበ። በሐዘን በእግሩ ሥርለተንበረከከችው እውነተኛ አማኝ ሲል ተወው እንጂ ሐቁን ይፋ ማውጣት ይችል ነበር።

“የሱስ «የት ነው የቀበራችሁት?» ብሎ በጠየቀ ጊዜ «ጌታ ሆይ! ና እይ» አሉት። ከዚያ ቀጥሎ ሁሉም ወደ መቃብሩ ሔዱ። አልዓዛር በጣም ተወዳጅ ስለነበር እህቶቹ አምርረው ሲያለቅሱና ወዳጆቹም ከሟቹ እህቶች ጋር በእንባ ሲራጩ ማየት በጣም አሳዛኝ ትእይንት ነበር በዚህ አስከፊ ሰብአዊ ስቃይ ምክንያትና የዓለም አዳኝ በአጠገባቸው እያለ ወዳጅ ዘመድ ሁሉ ስለሞተ ሰው ሲያለቅሱ ባየ ጊዜ “ኢየሱስም እንባውን አፈሰሰ።»

“ምንም እንኳን የእግዚአብሔር ልጅ ቢሆንም የሱስ ሰብአዊ ባሕርይን ስለተላበሰ በሰብአዊ ሐዘን ልቡ ተነካ። ለሚሰቃዩ ሁሉ ልቡ ርህሩህና አዛኝ ነው። ከሚያለቅሱ ጋር ያለቅሳል፣ ከሚደሰቱም ጋር ይደሰታል።”—The Desire of Ages, p. 533.

ሐ. በየሱስ ሕይወት ውስጥ ይህ አጋጣሚ ለእኛ ምሳሌ የሚሆንልን እንዴት ነው? ሮሜ 12፡15

“አስደናቂው የክርስቶስ ምሳሌ፣ ከሌሎች ሰዎች ጋር ሲሆን ስሜቶቻቸውን የተካፈለበት፣ ከሚያለቅሱት ጋር እያለቀሰ፣ ከሚደሰቱት ጋር አብሮ የሚደሰትበት ወደር የለሽ ርህራሄ፣ በቅንነት እርሱን በሚከተሉት ሁሉ ባህሪይ ላይ ጥልቅ ተጽእኖ ሊኖረው ይገባል። በዚያን ጊዜ በደግነት ቃላትና ድርጊቶች ለደከሙ እግሮች መንገዱን ቀላል ለማድረግ ይጥራሉ።”—The Ministry of Healing, pp. 157, 158.


ረቡዕ ፣ ሰኔ 18

4. ትብብር በእግዚአብሔር እና በሰው ልጆች መካከል

ሀ. የሱስ በዙሪያው ላሉት ምን ትእዛዝ ሰጣቸው? ዮሐንስ 11፡39 (የመጀመሪያ ክፍል)። ማርታ ምን ምላሽ ሰጠች እና የሱስ ምን አላት? ዮሐንስ 11፡39 (የመጨረሻው ክፍል)።

“ሁል ጊዜ አምላክ አንድ ነገር ለማድረግ ሲነሳ ሰይጣን የሚቃወም ሰው ያቀርባል። የሱስ «ድንጋዩን አንሱት» አለ። በተቻለ መጠን ለእኔ ሥራ ሁኔታዎችን አመቻቹልኝ ማለቱ ነው። ማርታ ግን በቀና አስተሳሰብዋ ጽኑ አቋም ነበራት። በመፍረስ ላይ የነበረው የወንድምዋ አካል እንዲታይፈቃደኛ አልነበረችም። ሰብአዊ ልብ የክርስቶስን ቃል ለማስተዋል ዳተኛ በመሆኑ ማርታ የክርስቶስን ተስፋ ትክክለኛ ትርጉም በእምነት መቀበል አዳገታት።

“«ካመንሽ የእግዚአብሔርን ክብር ታያለሽ ብየሽ አልነበረምን?» በማለት የሱስ ርጋታ በተሞላበት መንፈስ ማርታን ገሰጻት። ይህንም ሲል ለምን በእኔ ኃይል ትጠራጠሪያለሽ፣ እኔ አስፈላጊ ነው ከምለው ጋርየሚጻረር አስተሳሰብ ለምን ይኖርሻል፣ ቃሌ በእጅሽ ስላለልሽ ካመንሽ የእግዚአብሔርን ክብር ታያለሽ ማለቱ ነበር። ተፈጥሮአዊ ችግር የኃያሉን አምላክ ሥራ ሊገታ አይችልም። ጥርጣሬና አለማመን እንደ ትሕትና እይቆጠሩም። እውነተኛ ትሕትናና ራስን ማስገዛት ማለት ያለ አንዳች ጥርጣሬ በክርስቶስ ቃል ማመን ማለት ነው።

“«ድንጋዩን አንሡት» አለ የሱስ። ክርስቶስ ድንጋዩን ተነስ ብሎ ቢያዝዘው ትእዛዙን ባከበረለት ነበር። ወይም በአጠገቡ የነበሩትን መላእክት ድንጋዩን እንዲያነሱት ሊያዝዛቸው ይችል ነበር። ነገር ግን ድንጋዩ በሰው እጅ መነሳት ነበረበት። ይህን በማድረጉ የሱስ ሰብአዊ ፍጡራን ከመለኮት ጋር መተባበር እንዳለባቸው አሳየ። ሰው ሊሠራው የሚችለውን ነገርመለኮት እንዲሠራው መጠየቅ የለበትም። እግዚአብሔር የሰውን ትብብርይሻል። ሰው በተሰጠው ኃይልና ችሎታ እንደሠራ መጠን እግዚአብሔር ይተባበረዋል፣ ያበረታዋልም።”—The Desire of Ages, p. 535.

ለ. ዛሬ አለማመናችንን በእርጋታ የሚገስጸው የትኛው የክርስቶስ ቃል ነው? ዮሐንስ 11፡40

“ብዙዎች ሕያው እምነት የላቸውም። የእግዚአብሔርን ኃይል በበለጠ ሆኔታ የማያዩት ለዚህ ነው። ድክመታቸው የአለማመናቸው ውጤት ነው። . . . ያቅዳሉ እና ያዘጋጃሉ፣ ነገር ግን ጥቅት ይጸልያሉ፣ እንዲሁም በእግዚአብሔር ላይ ያላቸው እውነተኛ እምነት በጣም ትንሽ ነው። እነሱ እምነት እንዳላቸው ያስባሉ፣ ነገር ግን የሚያሳዩት ጊዜያዊ ሞቅታ ብቻ ነው፡፡ የገዛ ፍላጎታቸውን ወይም አምላክ ለመስጠት ፈቃደኛ ስለመሆኑ በትክክል ማስተዋል ባለመቻላቸው፣ ልመናቸውን በጌታ ፊት በትጋት በማቅረብ አይጸኑም።”—Christ’s Object Lessons, pp. 145, 146.


ሐሙስ ፣ ሰኔ 19

5. የሱስ አልዓዛር ከሞት አስነሳው

ሀ. የሱስ ከመቃብሩ አጠገብ ሆኖ ምን ጸሎት አቀረበ? ዮሐንስ 11:41፣ 42

“ክርስቶስ ባዘዘው መሠረት ድንጋዩ ተነሳ። ሁሉም ነገር ግልጽና ይፋ ሆኖ ተከናወነ። ምንም ዓይነት የማጭበርበር ነገር እንዳልተደረገ ሁሉም የማየት እድል ነበራቸው። አልዓዛር በሞት ኃይል ቀዝቅዞና ጸጥ እንዲል ተደርጐ በዋሻው መቃብር ውስጥ ይታይ ነበር። አልቃሾቹ ጸጥ ብለው በመቃብሩ ዙሪያ በመሰብሰብ የሚሆነውን ይጠባበቁ ነበር። …

“አሁን ክርስቶስ እግዚአብሔር አባቱ መሆኑን በመግለጽ በሙሉ ልብ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን አሳወቀ።”—The Desire of Ages, pp. 535, 536.

ለ. የሱስ አልዓዛርን ያስነሳው በምን ቃል ነው? ዮሐንስ 11፡43 ወዲያው ምን ሆነ? ዮሐንስ 11፡44

“[የክርስቶስ] ድምጹ ግልጽና ምንም ነገር የማያግደው ስለነበረ የሙቱን ጆሮ በስቶ ገባ። እርሱ በተናገረ ጊዜ መለኮት በሰብአዊነት ውስጥ ቦግ አለ። ሕዝቡ በእግዚአብሔር ክብር በበራው ፊቱ ላይ ኃይል እንደነበረው ለማረጋገጥ ቻሉ። ዓይን ሁሉ ወደ ዋሻው በር አተኮረ፣ ጆሮም ማንኛውንም ድምጽ ለማዳመጥ ተዘጋጀ። ከዚያ የነበሩት ሰዎች ሁሉ የክርስቶስን መለኮታዊነት ማስረጃ ለማየት በከፍተኛ ጉጉት ይጠባበቁ ነበር። ይህ ማስረጃ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን የሚያረጋግጥ ሲሆን ይህ ካልተሳካ ግን ተስፋ ለዘላለም ተደመሰሰ ማለት ነበር።

“ጸጥ ባለው መቃብር ውስጥ እንቅስቃሴ ታየ፣ ሞቶ የነበረው አልዓዛር በመቃብሩ በር ላይ ቆመ። … አሁንም በድጋሚ የሱስ ሰብአዊ ሠራተኛ ከእግዚአብሔር ጋር መተባበር እንዳለበት አሳያቸው። ሰው ለሰው መሥራት አለበት። አልዓዛር ተፈትቶ በሕዝቡ ፊት የቆመው በመካከለኛ እድሜ ላይ እንዳለ ጤነኛ ሰው እንጅ እንደ ደከመና እጅና እግሮቹ እንደሚንቀጠቀጡ ሕመምተኛ ሆኖ አልነበረም። ዓይኖቹ በማስተዋልና ለአዳኛችን በነበረው ፍቅር ይንጸባረቁ ነበር። በታላቅ አክብሮት በክርስቶስ እግር ሥር ወድቆ ሰገደ።”—Ibid., p. 536.


አርብ ፣ ሰኔ 20

የግል ግምገማ ጥያቄዎች

1. የአልዓዛር እህቶች በየሱስ ላይ ያላቸውን እምነት ግለጽ።

2. የሱስ ለማርታ፣ ለማርያም እና ለሁሉም አማኞች ምን ቃል ገብቷል?

3. የሱስ ያለቀሰው ለምንድን ነው?

4. በዚህ ተአምር የሰው ልጅ ከመለኮት ጋር እንዴት ተባበረ?

5. ለየሱስ ጥሪ አልዓዛር የሰጠውን ምላሽ ግለጽ።

 <<    >>